የአገሮችን ግንኙነት በባሕል መስክ ማጠናከር ያስፈልጋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

61

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) የአገሮችን ግንኙነት በባሕል መስክ ማጠናከር እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2005 ባጸደቀው የኅብረ-ባሕል መገለጫዎች ጥበቃና ልማት ሥምምነትን ኢትዮጵያ በ2008 መቀላቀሏ ይታወቃል።

ሥምምነቱ ኅብረ ባሕል የሰው ልጆች መገለጫ ባሕርይ መሆኑን በማረጋገጥ፣ የጋራ ቅርስ የያዘ፣ ለጋራ ጥቅም፣ እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በመረዳት የጸደቀ ነው።

እንዲሁም የሰው ልጆችን ምርጫዎች፣ ችሎታዎች እሴቶችን ጨምሮ የበለጸገና የተለያዩ የዓለም ፈጠራዎች ለኅብረተሰቡ፣ ለሕዝቦችና ለአገሮች ዘላቂ ልማት ዋነኛ ምንጭ መሆኑን በመገንዘብም የተደረሰ ነው።

ሥምምነቱን 146 አባል አገሮች የተቀበሉት ሲሆን፤ በሥምምነቱ አንቀጽ 9 መሠረት ኅብረ-ባሕል መገለጫዎችን ለጥበቃና ለልማት በየአገራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የወሰዷቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ በየአራት ዓመቱ ለድርጅቱ ሪፖርት ያቀርባሉ።

ኢትዮጵያ ሪፖርቱን በሚቀጥለው ሣምንት ለድርጅቱ ትልካለች።

ሪፖርቱን በሚመለከት ለዘርፉ አካላት ገለጻና ውይይት የተካሄደበት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባሕል ልማት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ተክሉ ለሪፖርቱ ዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንና የሪፖርት አርቃቂ አባላት ተሰይመው ረቂቅ ሪፖርቱ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

አገሪቱ የምታቀርበው ሪፖርት የኅብረ ባሕል መገለጫዎችን ለመጠበቅና ለማልማት፣ ባሕልን ለማበልጸግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ እኩልነትና መከባበርን ለማጠናከር የባሕላዊ ግንኙነት ዕድገትን ለማፋጠን ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

እንዲሁም በዓለም ሰፊና ሚዛናዊ፣ ተመጣጣኝ ልውውጦችን ማረጋገጥ፣ የመከባበርና የእርቀ- ሰላም ባሕልን ለማጠናከር በባሕሎች መካከል ውይይትን እንደሚያበረታታ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመድረኩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ቀደምት አገር ከመሆኗ አኳያ የበርካታ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት መሥራች መሆኗን አስታውሰዋል።

ሚኒስቴሩ ለዘመናት መንግሥት በመንግሥት ግንኙነት ላይ ብቻ አትኩሮ የነበረውን ዲፕሎማሲ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማዳበር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም አገሮችን በባሕል መስክ ለማቀራረብ ትኩረት መሠጠቱንም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

በዚህም በተለይ በባሕል መስክ ለሚደረገው ግንኙነት የሲቪክ ማኅበረሰቡ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ተዋናይ ናቸው ብለዋል።

አገሮች ተደጋግፈው እንዲያድጉ፣ እንዲበለጽጉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድም አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ በመስኩ ለሚከናወኑ ተግባራትም አጋር መሆኑንም  አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ አካላት አገሪቱ ያሏትን ኅብረ-ባሕላዊ መገለጫዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ተወዛዋዦች ጥበብ ማኅበር ፕሬዝዳንት መላኩ በላይ ሥምምነቱ የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግና አገሪቱንም ለመቀየር አቅም አለው ብሏል።

የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ ሥምምነቱ ለአገር፣ ለባለሙያዎችና ለሲቪክ ማኅበረሰቡ ውጤት እንደሚያስገኝ ገልጿል።

ኢኮኖሚያዊ ድጋፍን ለማግኘት፣ ዓለም አቀፋዊ አሠራሮችን ለመተግበር፣ ወጣቶችና ሴቶችን ለማብቃት፣ የባሕል ፖሊሲዎችን ለማጠናከር፣ አዳዲስ የንግድ ሞዴሎችን ለመፍጠር፣ የፈጠራ ሥራዎችን ያበረታታል ብሏል።

ሪፖርቱ በአጠቃላይ ቲያትር፣ በሲኒማ፣ ዲዛይን፣ በሚዲያ አርት፣ በሙዚቃ፣ በሥነ-ጽሑፍና በሥነ-ጥበብ ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም