የውስጥ አቅምን ለማጠናከር አገራዊ ገቢ መሰብሰብ ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

60

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2013(ኢዜአ) አገራዊ ገቢን በብቃት መሰብሰብና ለታመለት ዓላማ ማዋል የውስጥ አቅምን ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 በጀት ዓመት በስራቸው የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮችና ሠራተኞች የዕውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር አከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌውና የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር አገሪቷ ከተለያየ አቅጣጫ ጫናዎች እንዳሉባት አንስተዋል።

ከዚህ ጫናና ተፅዕኖ ለመላቀቅ የውስጥ አቅምን ማጠናከር አንገብጋቢ ጉዳይ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

ለዚህም ወሳኙ እርምጃም አገራዊ ገቢን በብቃት መሰብሰብና እያንዳንዱን ሣንቲም ለታሰበለት ዓላማ ማዋል እንደሆነ ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴርን አሰራር ማዘመን፣ ለታማኝ ግብር ከፋዮችና በዘርፉ ለሚሰሩ አካላት እውቅና መሰጠቱ ትልቅ እርምጃና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ተሸላሚዎቹንም አገራችሁን የምትወዱና የዜግነት ሃላፊነታችሁን የምትወጡ አርበኞች ናችሁ በማለት ይህንኑ ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው ለእውቅናና ሽልማት የበቁ አመራርና ሠራተኞችን በማመስገን ከተሸከሙት የአገርና የሕዝብ ሀላፊነት አንፃር እውቅናና ሽልማት አይበዛባቸውም ብለዋል።

አብዛኞቹ የገቢዎች ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞችና አመራሮች ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚታገሉ፣ አጭበሪባሪዎችና ግብር ሰዋሪዎችን የሚከለክሉ፣ የአገራቸው ሀብት እንዳይባክን የሚጠብቁ  አርበኞች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በ2013 በጀት ዓመት 290 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ይህን ለማሳካት አመራሩና ፈፃሚው ልምድና ዕውቀቱን በመጠቀም በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሸላሚ ሠራተኞች የተሰጣቸው እውቅና ለቀጣይ ስራቸውን መነቃቃትን እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

በስራ ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ላጡ ሠራተኞች ቤተሰቦችም ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቷል።

ለጉምሩክ አገልግሎት አስተዳደር በጎ አስተዋፅኦ የነበራቸው የጉምሩክ አስተላላፊዎችም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዕውቅናና ሽልማት ተቀብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም