ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትውልድን ከአደጋ መከላከል ያስፈልጋል --- ሚኒስቴሩ

57

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ አስተማማኝ ሰላምና ብልጽግና ግንባታ ትልም እውን ለማድረግ ትውልድን ከየትኛውም አደጋ መከላከል እንደሚያስፈልግ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ጤናማና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ሚዲያ ገንቢ ሚና እንዲጫወት ተጠይቋል።

ሚኒስቴሩ ከመንግሥትና የግል ሚዲያ ተቋማትና ከክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ኮቪድ-19 እየተከላከሉ ጤናማና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም በተያዘው የትምህርት ዘመን ጤናማና ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሣሙዔል ክፍሌ "የኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ አስተማማኝ ሰላምና ብልጽግና ግንባታ ትልም እውን ለማድረግ ትውልድን ከየትኛውም አደጋ መከላከል ይገባል" ብለዋል።

ኮቪድ-19ን እየተከላከሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ከሚዲያ ተቋማትና አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የሚዲያ አካላትም ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃን ለኅብረተሰቡ በማድረስ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ  ጠይቀዋል።

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሡ እንዳመለከቱት "አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሣሌት የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ምክንያታዊ ዜጋ ማፍራት ይጠይቃል"።

ለዚህም ሚኒስቴሩ፣ ሚዲያውና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቅንጅት በመሥራት አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ኮቪድ-19 እየተከላከሉ ትምህርትና ሥልጠናን ለማስቀጠል ሚኒስቴሩ ያዘጋጀውን የጥንቃቄ መመሪያ ለማኅበረሰቡ በማድረስ ሥጋትን መቀነስ ከሚዲያ ተቋማቱ ይጠበቃል።

መድረኩ ሚዲያው ትክክለኛና ተአማኒነት ያለው መረጃን ለማግኘትና በቅርበት ለመሥራት መነሻ እንደሚሆን ተገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮቪድ-19 እየተከላከሉ ትምህርትን ማስቀጠል እንደሚቻል መወሰኑን ተከትሎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከጥቅምት 23/2013 ጀምሮ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም