በሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን እየተሠራ ነው

116

ባሕርዳር፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን የተቀላጠፈ የወጭና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴን ለማስፈን እየተሠራ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የሩብ በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና ቅንጅታዊ አሠራርን በሀገሪቱ ለማዳበር የሚያግዝ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ  ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተጀምሯል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት በሩብ የበጀት ዓመቱ የትራንስፖርት ዘርፉ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የመሠረተ ልማትና የአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል።

ዘርፉን ለማዘመንም ብሔራዊ የትራንስፖርትና የሎጅስቲክ ፖሊሲዎች፣ የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎች ጸድቀው ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በተወሰኑ አካባቢዎች የሚካሄደውን የወጭና ገቢ ንግድ ለማስፋት በተከናወነው ሥራ የታጁራ ወደብ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው መጠናከር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

ክልሎች ከሚኒስቴሩ በሚወርደው አቅጣጫ መሠረት በትራንስፖርት ዘርፉ ለውጥ እየመጣ  የእግረኞችና የብስክሌት እንቅስቃሴ በከተሞች እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በሩብ የበጀት ዓመቱ የቢሮ አደረጃጀትን በመቀየር ለሠራተኞችና ደንበኞች ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር ባሻገር በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመሠረተ ልማት በመገንባት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መሠራቱን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዘርፉ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት የታጠቀ የሰው ኃይል ለመገንባት ሙያን መሠረት ያደረገ ተከታታይ የአቅም ግንባታ መከናወኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የጀርባ አጥንት መሆኑን አስረድተዋል።

ጥናቶች እንደሚያመላክቱትና መሬት ላይ ያለው እውነታ እንደሚያሳየው በሀገሪቱም ሆነ በክልሉ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሰውና ዕቃ የሚጓጓዘው በመንገድ ትራንስፖርት እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶክተር ፈንታ እንዳሉት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች በስፋት ወደ ሀገሪቱ  ከመግባታቸው ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ደህንነቱን የሚጠብቅ የትራንስፖርት አማራጭ የመጠቀም ፍላጎቱ እያደረገ ይገኛል።

ሆኖም ቀደም ሲል በነበረው ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ምክንያት ክልሉ የሚገባውን ድርሻ ካለማግኘቱም በላይ የሚገነቡ መንገዶች መጓተትና የጥራት መጓደል ችግሮች የሚስተዋሉበት እንደነበር ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን የመንገድ ተደራሽነትና ዘርፉን ለማሳደግ ያለውን እንቅፋት ፈጥኖ በማስተካከል ኅብረተሰቡ ተገቢውን  ጥቅም እንዲያገኝ በቅንጅት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በሩብ የበጀት ዓመቱ በዓበይት ተግባራት የታየው አፈጻጸም አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስካል ተክሌ ናቸው።

በመንገድ መሠረተ ልማት፣ ባቡር፣ ማሪታይምና ሎጅስቲክ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር 90 በመቶ መፈጸም መቻሉን  ጠቅሰዋል።

ይህም ለቀጣይ የመሥሪያ ቤቱ አፈጻጸም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረኩ በተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴን ጨምሮ ሌሎችም ከፌደራልና ክልሎች የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም