የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ የሚያስቆመን ኃይል የለም... የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት

54

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ የሚያስቆማት አንዳችም ምድራዊ ሀይል የለም ሲል የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዛሬ በላከልን መግለጫ እንዳለው የክልሉም ሆነ አጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝቦች በጋራ ጥረት የግድቡን ግንባታ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ አድርጎታል።

"የእለት ጉርስ ከሌለው ዜጋ ጀምሮ ሁሉም እንደየአቅሙ ያለውን እያዋጣ ከዳር እስከዳር በአንድ ድምጽ ሆ ብሎ በመነሳት ለግድቡ ግንባታ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል" ብሏል በመግለጫው።

ይህ ሀገራዊ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የክልሉ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ እንደማይታይ ያስታወቀው መግለጫው ይህ ህዝባዊ መነቃቃት የፈጠረው ቁጭት ነገ እንደሀገር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያቃልል በመረዳት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል።

ወደ እድገትና ብልጽግና በሚደረግ ጉዞ መቸም ቢሆን የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል ያለው መግለጫው ከሚገጥሙን ፈተናዎች ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት አንዱ መሆኑንን አስታውቋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንምፕ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷ አግባብ አለመሆኑን እና ግብፅም ግድቡን ልታፈርሰው እንደምትችል እንዲሁም ሀገራቸው የጀመረችውን እርዳታ ማቋረጡን እንደምትገፋበት መናገራቸው የሀገራችንን ህዝብ ያሳዘነ ተግባር መሆኑን መግለጫ አስታውቋል።

ለዚህ ተግባር ደግሞ የክልሉ ህዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚሰነዘረውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የክልሉ መንግሥት ገልጿል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ የሚያስቆመን አንዳችም ምድራዊ ሀይል ሊኖር አይችልም ያለው መግለጫው ግድባችንን በልበ ሙሉነት ጀምረነዋል አሁንም በተባበረ ክንዳችን በላብና በጥረታችን ገንብተን እናጠናቅቃለን ሲል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም