ተቋሙ በአገራዊ ምርጫው የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገለጸ

53

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በስድስተኛው አገራዊ ምርጫው የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 12 ቀን 2013 ባደረገው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አራተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ተቋሙ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን በዘንድሮው ምርጫ በሶስት ጉዳዮች ላይ እንደሚሳተፍ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

ተቋሙ በመንግሥት የሚወጡ ሕጎች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች በሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የተሰጣቸውን መብት እንደማይቃረኑ ክትትል ያደርጋል።

በዚህም መሰረት በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ የዜጎች የመምረጥ መብትን ጨምሮ የወጡ የምርጫ የሕግ ማዕቀፎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር አለመጻረራቸውን እንደሚከታተል ገልጸዋል።

ተቋሙ በማዕከልና በክልል ባሉት ስምንት ቅርንጫፎች ሰራተኞቹ 100ዎቹን በሥራው እንደሚያሰማራ ዋና እንባ ጠባቂው ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም በመጠቆም።

"ተቋሙ ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች ላይ 'አታስፈልጉም' በሚል በነበረው የፖለቲካ እምቢተኝነት ምንም ዓይነት ተሳትፎ አልነበረውም" ያሉት ዋና እንባ ጠባቂው፣ በዘንድሮው አገራዊ ምርጫው ላይ ''ጠንካራ ተሳትፎ'' እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነት ዓዋጅ ቁጥር 590/2000 ህብረተሰቡና መገናኛ ብዙኃን መረጃ የማግኘት ነጻነታቸው መከበሩን ይቆጣጠራል ብለዋል ዶክተር እንዳለ።

ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን ሐሳባቸውን ፍትሃዊ  በሆነ መንገድ ማቅረባቸውንና  መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ሚዛናዊ መሆናቸው እንደሚከታተል ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ሴቶች በምርጫው ላይ በምን አይነት መልኩ ተሳትፎ እያደረጉ ነው? በፖለቲካ ፓርቲዎችም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፉ ናቸው ወይ? የሚለው ጉዳይ ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

እስካሁን ተቋሙ በአገራዊ ምርጫው በታዛቢነት እንዲሳተፍ ጥሪ እንዳልተደረገለት ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥሪ ካቀረበለት ግን ለመታዘብ ዝግጁ ነው ብለዋል።

በምርጫ ሂደትና በውጤቱ ላይ ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ የሚበጅበት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ዶክተር እንዳለ አመልክተዋል።

ፍርድ ቤቶችም ለሚነሱ ቅሬታዎች ነጻና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ውሳኔ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ፓርቲዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሐሳባቸውን ለህብረተሰቡ ማቅረብ እንደሚገባቸው ዋና እንባ ጠባቂው አሳስበዋል።

በምርጫው የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ህብረተሰቡ ምርጫውን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም