በአፋር ክልል የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሀብት ምዝገባ እንደሚጀመር ተገለጸ

58

ሠመራ፣ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሀብት ምዝገባ በተያዘው የበጀት ዓመት ውስጥ እንደሚጀመር የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አብዱ ሳሊህ እንዳሉት የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሀብት ማስመዝገብና ማሳወቅ አዋጅ እንደሀገር ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ሆኖም በክልሉ አስፈላጊው የሕግ ማዕቀፍና የአዋጁ ተያያዥ ግብአቶች ባለመዘጋጀታቸው እስካሁን የሀብት ማስመዝገብ ሥራው እንዳልተጀመረ ጠቅሰዋል።

የሀብት ምዝገባ ታማኝነትና ግልጽነትን የሚያሳይ በመሆኑ እያንዳንዱ የመንግሥት ተሿሚ ምዝገባ ማካሄዱ ለግለሰቡም ጭምር ዘርፈ-ብዙ ጠቃሜታ አለው ብለዋል።

የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ በባለሙያዎች እንዲዘጋጅ በማድረግ በተያዘው የበጀት ዓመት አጋማሽ በሚካሄድ የክልሉ በምክር ቤት ጉባኤ ቀርቦ እንደሚጸድቅ የሚጠበቅ መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

እንደጸደቀም የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሀብት ምዝገባ እስከ አራተኛው ሩብ የበጀት ዓመት ለመጀመር ኮሚሽኑ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ካስመዘገቡት ሀብት ውጭ ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው የመንግሥት ንብረት ለግል ጥቅም እንዳይውል ለመከላከል እንደሚረዳ ጠቁመው በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ግልፅነትና መተማመን ከፍ እንደሚያደርገውም አመልክተዋል።

ለሥራው እንዲረዳም የልምድ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው በተጓዳኝም የምዝገባ ሥራውን ለማከናወን የባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም