የቻይና 2 ግዛቶችና ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሶችን ድጋፍ አደረጉ

88

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13/2013 ( ኢዜአ) በቻይና የሚገኙ ሁለት ግዛቶች እና የቻይና ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ የተለያዩ ቁሶችን ለኦሮሚያ ክልል ድጋፍ አደረጉ።

የቻይና ጂያንግሱ፣ ኒንጃንግ እና የቻይና ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ በዛሬው ዕለት ድጋፍ ያደረጉት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ 20 የመተንፈሻ አጋዠ መሳሪያዎች፣ 5 ልዩ  የመተንፈሻ አጋዠ መሳሪያዎች፣  350 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም 4 ሺህ የህክምና ልብስ ናቸው።

በቁሳቁስ ድጋፉ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሸመልስ አብዲሳ እና በቻይና ኢምባሲ የኢኮኖሚና ኮሜርስ ካውንስለር ሚኒስትር ሚሲስ ሊ ዩ ተገኝተዋል።



በርክክቡ ላይ ሚሲስ ሊ ዩ " የቻይና መንግስት ኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የቴክኒካል እና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንዲገነባ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንና በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

"በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች አገሪቱን እንደ ሁለተኛ አገር በመቁጠር የተለያዩ ድጋፎች ከማድረግ በተጨማሪ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብአቶችንና መሳሪያዎችን እያመረቱ ይገኛሉ" ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሸመልስ አብዲሳ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የቻይና ኢንቨስተሮች በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም  ተጨማሪ መዋለንዋይ በክልሉ እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም