መገናኛ ብዙሃን ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት አጀንዳ ቀርጸው እንዲደግፉ ተጠየቀ

75

ሀዋሳ ጥቅምት 13/2013 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መላው ህብረተሰብ ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት በጋራ እንዲሰለፍ አጀንዳ ቀርጸው በሙያቸው እንዲደግፉ ተጠየቀ። 

በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ልማት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት  ባለሙያዎች የተዘጋጀ የግንዛቤ ማበልፀጊያ ስልጠና በሀዋሳ ከተማ እየተሰጠ ነው።

አዘጋጁ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መብራቴ ተክለማርያም እንደገለጹት ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ የመንግሥት፣ ባለሀብቶችና የህዝቡ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል።

ይህን እውን በማድረግ በኢንዱስትሪ የዳበረችና የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር መንግሥት ስትራቴጂ ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎች በስትራቴጂው ዙሪያ ግንዛቤ  በመፍጠር መላው ህብረተሰብ ለኢንዱስትሪ ልማት በጋራ እንዲሰለፍ  አጀንዳ ቀርጸው በሙያቸው እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

በተለይ የኢንዱስትሪው ልማት ስትራቴጂው ዋና ሞተር የግል ባለሀብቱ በመሆኑ  ቀጥተኛ ድጋፍ እንዲያገኝም እንዲሁ።

ለኢንዱስትሪ ልማት መፋጠን አርሶ አደሩ መረባረብ አለበት ያሉት ኃላፊው በዚህ ረገድ ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በጥራትና በስፋት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ በበኩላቸው በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ካሉ ክፍተቶች መካከል ዘርፉ ለሃገራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ላይ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ባማከለ መልኩ የመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት  ሽፋን አለመስጠት ዋንኛው እንደሆነ ተናግረዋል።

በዘርፉ ልማት ዙሪያ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳራቶችን ነቅሶ ከመጠቆም ረገድም ሰፊ ውስንነት እንዳለ አመላክተዋል።

በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለማቃለል ከመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት አካላት ጋር ቋሚ  የአሰራር ግንኙነት ለመፍጠር ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በቀጣይ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የብልፅግና መንገድ መሆኑን ማስገንዘብ፣ ለዚህም ከአነስተኛና መካከለኛ የሚጀመር እድገት መሆኑን ማሳወቅ ከመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት  ባለሙያዎች እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

በተለይ ወጣቶች ወደ አምራች ዘርፍ በስፋት እንዲቀላቀሉ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም ማህበረተሰቡ የሀገሩን ምርት የመጠቀም ባህሉን እንዲያሳድግና በምርት እሴት ሠንሰለት ውስጥ የሚፈጠረውን የተጠቃሚነት ትስስሮች ማጉላት ለዘርፉ መበልፀግ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ መስፋፋት ለብዙ የስራ እድል በር ከፋች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በመድረኩ  በእንግድነት የተገኙት የሲዳማ ክልል የስራ እድል ፈጠራ፣ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ ሞላዶ ናቸው።

በተለይ የውጭ ገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ  አቅማቸውን ለማሳደግ ዓይነተኛ ጠቀሜታ ስላለው ለዘርፉ ማደግ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ  አመልክተዋል።

ለሶስት ቀናት በተዘጋጀው የስልጠናው መድረክ ከፌዴራልና ክልሎች የተወጣጡ የመገናኛ ብዙሃንና ህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም