በአማራ ክልል ውሃ በማቆር ከ56 ሄክታር በላይ አዲስ መሬት በበጋው ለማልማት እየተሰራ ነው

102
ባህር ዳር ሀምሌ 9/2010 በአማራ ክልል በክረምት የሚጥለውን የዝናብ ውሃ በማቆር በመጭው በጋ ከ56 ሄክታር የሚበልጥ አዲስ መሬት ላይ የአነስተኛ መስኖ ልማት ለማካሄድ የሚያስችል ሥራ መሰራቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የመስኖ ልማትና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ኢንጀነር እንዳገር ጌትነት ለኢዜአ እንደገለጹት ከ600 በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብና ጆኦመብሬን የለበሱ ኩሬዎች ተዘጋጅተዋል። ከተዘጋጁት ኩሬዎች ውስጥ 556 ጆኦመብሬን የለበሱ ኩሬዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ማህበረሰቡ በጋራ የሚጠቅማበቸው ኩሬዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት የዝናብ ውሃ እቀባ ሥራው እየተከናወነ ያለው ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ነው። ባለፉት ዓመታት 45 ሺህ 986 ነባር የጂኦመብሬን ኩሬዎችን በመጠቀም 2ሺህ 108 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ጠቁመው በዚህ ዓመት ውሃ የሚይዙት ኩሬዎች ቁጥር ሲጨመር የአርሶ አደሩ ተጣቀሚነት እያደገ እንደሚመጣ አመልክተዋል። ድርቅ የሚያጠቃቸውን ሁሉንም አካባቢዎች ተጠቃሚ ለማድረግም በየዓመቱ የክልሉ መንግስት በሚመደበው የካፒታል በጀት ልክ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ኢንጂነር እንዳገር አስረድዋል። በመጪው ዓመትም ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ 446 የተለያዩ የውሃ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ ከወዲሁ ይፋ መደረጉንም ነው የገለጹት። ከሚከናወኑ የውሃ ማሰባሰብ ስራዎችም  አነስተኛ የግድብ ስራ፣ የማህበረሰብ ኩሬ፣  ምንጭ ማጎልበት ፣ የወንዝ ጠለፋ እና የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል። በጀቱም ከክልሉ መንግስት፣ የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት(ኢፋድ)፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራም እና የግብርና እድገት ፕሮግራም የተገኘ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በዕቅዱ መሰረት የውሃ ማሰባሰብ ሥራዎች በሁሉም የክልሉ ዞኖች የሚከናወኑ ሲሆን በእዚህም 100 ሄክታር መሬት በአነስተኛ መስኖ እንዲለማ ከማድረግ ባለፈ ውሃው ለሰውና ለእንስሳት መጠጥ አገልግሎት ይውላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም