የልዩ ዘመቻዎች ሀይል ስልጠና በሀገር ላይ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ነው...ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ

123

ጥቅምት 12/2013(ኢዜአ) የልዩ ዘመቻዎች ሀይል ስልጠና በቀጣይ በሀገር ላይ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማዘዣ በአምስት ሻለቃ ያሰለጠናቸውን የኮማንዶ አባላትን የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል።

ስልጠናውን የወሰዱት የኮማንዶ አባላት ልዩ ልዩ ግዳጆችን የሚወጡ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻ ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፤ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ስልጠና በአገር ላይ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ነው።

"ስልጠናው እንደ ሀገር በቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት መከላከልና መወጣት እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነው" ሲሉም አስረድተዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ስልጠናው ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋን በመቋቋም ግዳጅን መወጣት የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።

የአለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የሽብር ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል ብሎም በከተሞችና ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ተልዕኮን ለመወጣት እንደሚያስችልም ዋና አዛዡ አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት “የሀገር ዋልታ፤ የህዝብ አለኝታ” መሆኑን አንስተው፤ ሠላምንና የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሰራ ኃይል መሆኑንም ተናግረዋል።

በልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማዘዣ የተሰጠው ስልጠና አንድ ሻለቃ ኮማንዶ የሪፐብሊካን ጋርድ፤ ሁለት ሻለቃ ልዩ ኃይል ፤ አንድ ሻለቃ የጸረ ሽብር ልዩ ኃይል እንዲሁም አንድ ሻለቃ የፌደራል ፓሊስ ኮማንዶን የያዘ ነው።

በነገው እለትም በልዩ ዘመቻዎች ሀይል የሰለጠኑ የአየር ወለድ ኮማንዶ አባላት የተለያዩ ትርኢቶችን ያሳያሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም