ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ተፈጸመ

59

ደሴ፣ጥቅምት 12/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል የተለያዩ አደረጃጀቶችን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ገዙ።

የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት የተፈጸመው የቦንድ ግዥው የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ተከትሎ በተፈጠረ መነሳሳት ነው።

የወጣት፣ ሴቶችና ሌሎች አደረጃጀቶች እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የተፈጸመ የቦንድ ግዥ መሆኑንም አመልክተው የህዳሴ ግድቡ እስኪጠናቀቅም ህብረተሰቡን በማስተባበር ቀጣይነት ያለው የቦንድ ግዥ ለማካሄድ የተጀመረው ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቦንድ ግዥ ከተፈጸመው ውስጥ በክልሉ የሚገኙ ወጣቶችን በማስተባበር የተከናወነ አምስት ሚሊዮን 500ሺህ ብር እንደሚገኝበት የገለጸው ደግሞ የክልሉ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ ነው።

ይህም የክልሉን ወጣቶች በማሳተፍ ከ50 ብር እስከ 300 ብር ቦንድ እንዲገዙ በታቀደው መሰረት እንደተከናወነ ጠቅሶ ይሄው ተግባር እስከ ጥር 30/2013 ዓ.ም አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኢብራሂም በበኩላቸው ሴቶችን በየደረጃው በማስተባበር አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የእጅ በእጅ ቦንድ ግዥ መፈጸሙንና ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ደግሞ ቃል መገባቱን አስታውቀዋል።

በከተማው ሴቶች ሊግ አስተባባሪነት የአንድ ሺህ ብር ቦንድ መግዛቷን የተናገረችው ደግሞ በደሴ ከተማ የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፋጡማ ሰይድ ናት፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ  የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም