በመተከል ዞን የአኩሪ አተር የዘር ብዜት የሚያከናውኑ ወጣቶች የትራክተር ችግር እንደገጠማቸው ገለጹ

57

አዲስ አበባ   ጥቅምት 12/2013 (ኢዜአ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ተደራጅተው የአኩሪ አተር የዘር ብዜት የሚያከናውኑ ወጣቶች የትራክተርና የመውቂያ ማሽን ችግር እንደገጠማቸው ገለጹ። 

ወጣት በላይ ማንጉዋኬና ወጣት ንግስት አማረ በክልሉ ማንዱራ ወረዳ አይዲዳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

ወጣቶቹ እንደሚሉት 35  ወጣቶች በመደራጀት በተሰጣቸው እርሻ ከፓዊ ግብርና ምርምር ማዕከል በቀረበላቸው የአኩሪ አተር ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ ወደ ስራ ገብተዋል።

የምርምር ማዕከሉ የአኩሪ አተር ዘርንና የባለሙያ ክትትል  ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘንድሮው ዓመት በ32 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ አኩሪ አተር የዘሩ ሲሆን አሁን ላይ ለአጨዳ ደርሷል።

በፓዊ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘውን 'ፓዊ-2' የአኩሪ አተር ዝርያ በማብቀል በሄከታር እስከ 30 ኩንታል እንደሚያገኙ ይጠበቃሉ።

ወጣቶቹ በቀጣይ ማሳቸውን የማስፋት ዕቅድ ቢይዙም የማረሻ ትራክተርና የመውቂያ ማሽን ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ክረምት የእርሻ ወቅት ትራክተር በማጣት ተቸግረው እንደነበር አስታውሰው፣ መንግስት በቀጣይ ትራክተር ና የውሃ መሳቢያ ጀነሬተር እንዲሟላላቸው ጠይቀዋል።

በቀበሌው የሰብል ባለሙያ አቶ መላኩ ፈንታ እንዳሉት በ2012/2013 የምርት ዘመን 751 ሄክታር ማሳ በአኩሪ አተር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 32 ሄክታሩ በተደራጁ ወጣቶች የተዘራ ነው።

የአኩሪ አተር ምርት ተፈላጊነት እያደገ በመምጣቱ አርሶ አደሩ በብዛት እያመረተ መሆኑን ገልጸው ቀበሌውም ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር መሬት እያቀረበ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም