የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የ2020/21 ውድድርን ማንችስተር ዩናይትድ፤ባርሴሎና እና ጁቬንቱስ በድል ጀምረዋል

168

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የ2020/21 የውድድር አመት ትንናት ሲጀመር ታላላቆቹ ማንችስተር ዩናይትድ፤ባርሴሎና እና ጁቬንቱስ በድል ጀምረዋል።

የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ በነበረው የፓሪስ ሴንት ጀርሜን እና ማንችስተር ዩናይትድ ፍልሚያ ከሜዳ ውጪ በተጫወተው ማንችስተር ዩናይትድ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ማንችስተር ዩናይትድን ለድል ያበቁ ግቦችን በምሽቱ ጨዋታ አንበል የነበረው ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ23 ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እና ማርከስ ራሽፎርድ በ87ኛ ደቂቃ በጨዋታ አስቆጥረዋል።

ለፓሪሱ ክለብ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው የዩናይትዱ አጥቂ አንቶኒ ማርሲያል በራሱ ግብ ላይ ነው።

በአዲሱ የውድድር አመት ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ማንችስተር ዩናይትድ በምሽቱ ጨዋታ ተሽሎ ተገኝቷል።

የፈረንሳዩ ግዙፍ ክለብ በቫምፒዮንስ ሊጉ በሜዳው በተከታታይ ሁለት ጊዜ በማንችስተር ዩናይትድ ተረቷል።

የዛሬ ሁለት አመት በ2018ቱ የቻምፒንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ሁለት ለአንድ በሆነ ዉጤት ሲያሸንፍ ማርከስ ራሽፎርድ ያኔም የማሸነፊያ ግቧን አስቆጥሯል።

ባለፈው አመት በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ ደርሶ የነበረው ፓሪስ ሴንት ጀርሜን፤ በሜዳው በተደረገ የምድብ ጨዋታ ሲሸነፍ እአአ 2004 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሌሎች ትናንት ምሽት በተከናወኑ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች የሃንጋሪውን ፈረንቫሮስ ክለብ ያስተናገደው ባርሴሎና አምስት ለ አንድ በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።

በዚህ ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ፤ወጣቱ አንሱ ፋሰቲ ፤ፊሊፔ ኮቲንሆ፤ዴምቤሌ፤ፒኬ እና ጎንዛሌዝ ለካታሎኑ ክለብ አስቆጥረዋል።

ያለ ክርስቲያኖ ሮላንዶ ወደ ዩክሬን ተጉዞ ዳይናሞ ኪዬቭን የገጠመው ጁቬንቱስ በበኩሉ አልቫሮ ሞራታ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ከሜዳው ውጪ ድል አድርጓል።

ቼልሲ እና ሴቪላ በስታንፎርድ ብሪጅ ያደረጉት ፍልሚያ ያለ ምንም ጎል ባዶ ለባዶ ሲጠናቀቅ፤ላዚዮ ቦሩሲያ ዶርትመንድን ሶስት ለአንድ፤አርቢ ሌብዚግ የቱርኩ ኢስታሰንቡል ባሳክሴርን ሁለት ለባዶ፤ሬኔስ ከክራስኖዳር አንድ እኩል እና ክለብ ብሩጅ ከሜዳው ውጪ የሩሲያውን ሴንት ፒተርስበርግን ሁለት ለአንድ ያሸነፈበት ጨዋታ በምድብ 5-8 ውስጥ የተደለደሉ ክለቦች የትናንት ምሽት መርሃ ግብሮች ናቸው።

ዛሬም ጨዋታዎች ሲወቀጥሉ የአምናው አሸናፊ ባየር ሙኒክ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፤ማንችስተር ሲቲ ከፖርቶ፤አያክስ ከሊቨርፑል፤ሪያል ማድሪድ ከ ሻካታር ዶኔስክ፤ኢንተር ሚላን
ከ ቡሩሲያ ሞንቼግላድባህ፤ኦሊምፒያኮስ ከ ማርሴይ ፤ሳልስቡርግ ከ ሎኮሞቲቭ ሞስኮው እና ሚድትጅላንድ ከአትላንታ ይጫወታሉ።

ምንጭ፤ቢቢሲ ስፖርት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም