ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝን በመቋቋም ሰው ተኮር የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧ ተገለጸ

56

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽሽን መቋቋም የሚችል ሰው ተኮር የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን የኢፌዴሪ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የተናበበ የኢኮኖሚ አስተዳደር ለዕድገቱ መመዝገብ ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ አስመልክቶ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ውይይቱን ያደረጉት የኮሚቴው አባላት የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአለምአቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ስጋት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝ ተቋቁማ የ6 ነጥብ አንድ በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ነው በውይይታቸው ያነሱት።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ እንዳሉት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ የተናበበ የኢኮኖሚ አስተዳደር መፈጠሩ የቫይረሱን ተጽዕኖ መቋቋም አስችሏል።

ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠርና ለአርሶአደሩ ገበያ በማፈላለግ በኩልም ዕድገቱ ጉልህ ሚና ነበረው ብለዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ይመዘገቡ የነበሩ ውጤቶች ሰው ተኮር እንዳልነበሩ ነው ያነሱት።

ዕድገቱ የሰውን ህይወት በተጨባጭ የቀየረ ባለመሆኑም ትችት ይነሳበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በ2012 ዓ.ም የተመዘገበው ውጤት ግን የኮሮና ወረርሽኝን የተቋቋመና ሰው ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ላስመዘገበችው የ6 ነጥብ አንድ የኢኮኖሚ ዕድገት የፋይናንስ ዘርፉ ጉልዕ ሚና ነበረው ብለዋል።

የባንኮችን ቅርንጫፍ በማስፋፋት የቁጠባ ሂሳብን ማሳደግ መቻሉንም አስታውቀዋል።

እንደ ኮሚቴዎቹ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ አሁን እያስመዘገበችው ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ በ2013 ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን እቅድ ታሳካለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም