ኢንዱስትሪዎች በምርታቸው የገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ድጋፍ እየተደረገ ነው

71

አዳማ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) ኢንዱስትሪዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ማስፋፊያ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ ጋር በመሆን ለአስሩ  ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች  በምርት ጥራት አጠባበቅ ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ  ተካሄዷል።

በመድረኩ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ወልደማሪያም አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲያመርቱና በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ጨርቃ ጨርቅ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ፣ ቆዳ፣ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ዘርፎች ለተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች  ድጋፍ ከሚሰጣቸው መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ቀደም ሲል  ደረጃ የወጣላቸውንና አዲስ የሚወጣላቸው ምርቶች የተሻለ ጥራት ኖሯቸው በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የገቢ ምርቶችን መተካት እንዲችሉ ከደረጃዎች ኤጄንሲ ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

በክልሎችና  ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ዝቅተኛውን ዓለም አቀፍ የምርት ጥራት ደረጃን አሟልተው እንዲያመርቱ ተከታታይ ድጋፍ እየተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ የአቅም ግንባታ፣ የሙያና ቴክኒካዊ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ለከተሞችና ክልሎች የኢንዱስትሪ ቢሮዎች፣ አምራች እንዱስትሪዎች ድረስ ይሰጣል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ የደረጃ ትግበራ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተፈራ በበኩላቸው በሁሉም የአገልግሎትና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የጥራት ደረጃ ማሟላት ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርት ጥራትና ደረጃ አወሳሰን ለተጠቃሚውና ለዋጋ ብቻ ሳይሆን አምራቾች ለህልውናቸው ሲሉ መተግበር ያለባቸው ነው ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞችና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች፣ ምግብና አግሮ ፕሮሰሲንግ ድረስ  የምርት ጥራት ለማስጠበቅ ከቴክኒካዊ ድጋፍ ጀምሮ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

እስካሁን ከ12ሺህ በላይ ደረጃዎች መዘጋጀታቸውን  የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ከወቅቱ የገበያ ውድድርና ጥራት ጋር የማይሄድ ካለ እየተሰረዘና በአዲስ እየተተካ እየተተገበረ ይሄዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም