የመተከልን ሠላም ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመተከልን ሠላም ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ ነው
አሶሳ፣ ጥቅምት 10/2103(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞንን ጸጥታ ወደ ቀደመ ሠላሙ ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱላዘዚ መሐመድ አስታወቁ፡፡
በዞኑ ጉባ ወረዳ ባለፉት አራት ቀናት በተደረገ ኦፕሬሽን 27 ሽፍታዎች መደምሰሳቸውም ተገልጿል፡፡
ኮሚሽነሩ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት መተከል ዞን ከግጭት ወጥቶ ወደ ቀደመ ሠላሙ እየተመለሰ ነው፡፡
የሃገር መከላከያና ሌሎችም የጸጥታ አካላት በዞኑ ግጭት ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች ጨምሮ ሰባቱንም ወረዳዎች በቁጥጥር ስር አድርገዋል ብለዋል፡፡
የጸጥታ ኃይሉ የተጠናከረ ዘመቻ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽነር አብዲላዚዝ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቁሳቁስ እና ሌሎች ግብዓቶች የሚጓጓዙበት ከዳንጉር ወረዳ ማምቡክ እስከ ጉባ ወረዳ ከተማ ማንኩሽ ያለው መንገድ በጸጥታ ኃይሉ ጥብቅ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት አራት ቀናትም የጸጥታ ኃይሉ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በጉባ ወረዳ ባደረገው አሰሳ 27 የጥፋት ኃይሎች ተደምስሰዋል ብለዋል፡፡
ሌሎች ሰባት የጥፋት ኃይሉ አባላት እና ተባባሪዎቻቸው መማረካቸውን አመልክተው 34 የጦር መሣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋሉን አስረድተዋል፡፡
በመተከል ዞን ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እስከዛሬ 567 መድረሱን ኮሚሽነር አብዱላዘዚ አስታውቀዋል፡፡
የጥፋት ኃይሉ ተልዕኮ የህዳሴውን ግድብ ማስተጓጎል እንደሆነ ጠቁመው ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ስልት ያደረጉት የመተከል ዞን ህዝብ እርስ በርስ በማጋጨት ትርምስ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
በሃገር ውስጥ እና ውጭ በሚገኝ አካላት የሚደገፈው የጥፋት ኃይሉ ወታደራዊ ስልጠና ጭምር በመውሰድ ድንበር አቋርጠው እንደገቡ የተደረሰበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የህግ የባላይነትን ማስከበሩን እንደሚቀጥል የገለጹት ኮሚሽነሩ የጸጥታ ኃይሉ የጀመረውን ኦፕሬሽን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የአካባቢውን ሠላም ሙሉ በሙሉ እንደሚመልስ አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመተከል ዞን ከሐምሌ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ጸረ ሰላም ኃይሎች አካባቢውን በማወክ ሲፈጥሩ በነበረው ችግር የሰዎች ህልፈት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆናቸው ተመልክቷል፡፡