በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

105

ሀዋሳ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ) በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጠየቀ።
በቢሮው የ2012 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የተያዘው ስራ ዘመን ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር  የባለድርሻ አካላት መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ በቢሮው የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወይዘሮ ወሰን ግዛቸው ኮሮናን ለመከላከል ቤት ውስጥ መቆየት ወሳኝ ቢሆንም በዚህ ሂደት በሴቶችና ህፃናት ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም  ተናግረዋል።

ይህም ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችና ለህልፈት የሚዳርጉ በመሆናቸው ተግባሩን ማስቆም ልዩ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን አቀናጅቶ መምራትና በእቅድ በማካተት ለውጤታማነቱ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በተለይ ሁሉን አቀፍ የተቀናጀና የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ማጠናከርና ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ መሆኑም ተመልክቷል።

ይህም በተደራጀ አግባብ የህግ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምናና ተያያዥ ማስረጃዎችን ከማቅረብ ባሻገር ተጎጂዎች ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ጥቃቱ የሚያስከትልባቸውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው  የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ሊጠናከሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይ በክስ ወቅት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች፣ ፍትሃዊ፣ ፈጣንና ተገቢ ምላሽ መስጠት፣ ወጥነት የተከተለ አሰራርን መከተል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት የሚቀርቡ መረጃዎች የተሟሉና ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ  በማድረግ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲቆም በጋራ መረባረብ እንደሚገባም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም