በደብረ ብርሃን ከተማ ከ50 ኩንታል በላይ የተበላሸ በርበሬ በወፍጮ ቤት ተያዘ

149
ደብረብርሃን ግንቦት 1/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ከ50 ኩንታል በላይ የተበላሸ በርበሬ በአንድ ወፍጮ ቤት ተከማችቶ መያዙን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ። የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ታየ ኃብተጊዮርጊስ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የተበላሸው በርበሬ በቁጥጥር ስር የዋለው ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ነው። በቀበሌ 02 በሚገኝ አንድ ወፍጮ ቤት ለመፍጨት ሲዘጋጅ በህብረተሰቡ ጥቆማ የተያዘው የተበላሸና ለሰው ልጅ ጤና አደገኛ የሆነ በርበሬ ከ50 ኩንታል በላይ እንደሆነም አመልክተዋል። በመሆኑም በርበሬውን ለማስፈጨት በማዘጋጅት ላይ የነበረች አንዲት ሴትና የወፍጮ ቤቱ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ለጊዜው የተሰወረውን የወንጀሉ ዋነኛ ተዋናይ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ ጤናን የሚጎዱ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት ተገቢውን ጥቆማ መስጠት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም