በጋምቤላ ክልል ለተጀመረው የትምህርት ስራ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

78

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን መከላከልን ታሳቢ በማድረግ ለተጀመረው የመማር ማስተማር ሥራ ውጤማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።


በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ትምህርት በክልሉ በሚገኙ የገጠር ትምህርት ቤቶች ትናንት ተጀምሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ  በጋምቤላ ወረዳ ቦንጋ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የትምህርት ስራውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት ለመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ግንባር ቀደም  ኃላፊነት አለባቸው።

በተለይም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ተማሪዎች ትምህርታቸውን ያለ ስጋት እንዲከታተሉ ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ በገጠር ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የመማር ማስተማር ስራ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በከተማም ለማስቀጠል  በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ ተከስቶ በነበረው ጎርፍ ጉዳት በደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን የማስተካከያና  ኮሮናን ለመከላከል የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በማሟላት ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ጭምር አመራሩ ያለመታከት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት ለተጀመረው የመማር ማስተማር ስራ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጓነር ማጆክ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቀመጠውን መስፈርት ባሟሉ በርካታ የገጠር ትምህርት ቤቶች ትናንት የማስተማር ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም በከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊው መስፈርትና ግብዓት በማሟላት ከጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተለይም ከትምህርት ሚኒስቴር በድጋፍ የተገኘውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል  ጨምሮ ውሃና ሌሎች ግብዓቶች በትምህር ቤቶች እየተሟሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኮሮና ቫይረስን በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  የቦንጋ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ምክር ገለጠ ናቸው።

ባለፈው ዓመት የባከነውን የትምህርት ጊዜ በማካካስ  ተማሪዎች ለማብቃት ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ አቡላ አኳይ በሰጠው አስተያየት በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ትምህርት በመከፈቱ መደሰቱን ገልጿል።

ባለፉት ወራት ልጃቸው ትምህርት አቋርጦ በመቆየቱ ተቸግሮ እንደነበር የተናገሩት የቦንጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኡሞድ አጃክ ናቸው።

አሁን ላይ ግን ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቁመው፤ ለትምህርት ስራው መቃናት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበረከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል 400 በሚጠጉ የአማራጭ፣ የቅደመ መደበኛ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 179 ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም