በአዳማ ከተማ ህንጻ ተደርምሶ የአራት ሰው ህይወት አለፈ

39

አዳማ፣ ጥቅምት10/2013(ኢዜአ) በአዳማ ከተማ ዛሬ ህንጻ ተደርምሶ ባደረሰው አደጋ የአራት ሰው ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በአዳማ ደምበላ ክፍለ ከተማ ኢሬቻ ቀበሌ ውስጥ ነው።

በቀበሌው ልዩ ስሙ ኮሮኔል ደጀኔ ስሜ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ያለው ሃዊ ሆቴል በመደርመሱ አደጋው  ሊደርስ  እንደቻለ አስረድተዋል።


ሆቴሉን በአዲስ ህንፃ ለመተካት አሮጌውን እያፈረሱ ባሉት የቀን ሠራተኞች ላይ በደረሰው አደጋ ከመካከላቸው የአራት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን ኢንስፔክተሯ አስታውቀዋል።


ሁለት ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የአደጋው መንስኤ የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም