ከ60 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የዴፖ ውስጥ ነዳጅ ማደያዎች ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ

67

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከታፍ ኦይል ጋር በመተባባር ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባቸው የዴፖ ውስጥ ነዳጅ ማደያዎች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

ማደያዎቹ ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ ባለፈ የድርጅቱን አገልግሎት የተሳለጠ ያደርጋሉ ተብሏል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እና የታፍ ኦይል ፕሬዚዳንት አቶ ትንሳኤ አክሊሉ የዴፖ ውስጥ ነዳጅ ማደያዎቹን ትናንት መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።

የድርጅቱ ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ ፍሬህወት ትልቁ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ አራት የድርጅቱ የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎች ውስጥ ባሉ ዴፖዎች እየተገነቡ ካሉት ነዳጅ ማደያዎች መካከል ሁለቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

በጀሞና አስኮ አካባቢዎች በሚገኙ ሁለቱ ዴፖዎች ውስጥ ለተገነቡ ነዳጅ ማደያዎች የግንባታ ሥራም ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አመልክተዋል።

የድርጅቱ ተሽከርካሪዎች በሚያድሩባቸው ቦታዎች (ዴፖዎች) የተገነቡት ነዳጅ ማደያዎቹ የድርጅቱ አውቶቡሶች ነዳጅ ለመቅዳት ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ይባክን የነበረውን ጊዜና ጉልበት ከማስቀረት ባለፈ ህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት በወቅቱ እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ለበርካታ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በራሱ ዲፖዎች ነዳጅ ማደያዎች መገንባቱ ጊዜና ገንዘብ እንደሚቆጥብ የገለጹት ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።

ማደያዎቹ ድርጅቱ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሳለጠና ተደራሽ እንድሚያደርገውም አመልክተዋል።

ነዳጅ ማደያዎቹ ለድርጅቱ ካላቸው ጠቀሜታ ባለፈ ለሌላው ህብረተሰብም አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው ለትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚኖራቸው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ ሁለት ዴፖዎች በዊንጌት እና አቃቂ አካባቢዎች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም