የበረሃ አንበጣን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምስራቅ አፍሪካ አገራት በትብብር መስራት ይገባቸዋል... የዘርፉ ምሁራን

75

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) የበረሃ አንበጣን ከመነሻው ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምስራቅ አፍሪካ አገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የበረሃ አንበጣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እና በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በምን አይነት መልኩ ቢሰራ በቀላሉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይችላል በሚል የግብርና ዘርፍ ተመራማሪ ባለሙያዎችን ጠይቋል፡፡

ምሁራኑም የበረሃ አንበጣ አህጉራዊና ድንበር ዘለል ወረርሽኝ በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገራት ከመነሻው ለመከላከልና ለመቆጣጠር በገንዘብና በቁሳቁስ የተደራጀ ተቋም ገንብተው በትብብር መስራት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

የአፍሪካ ነፍሳት ሳይንስ ለምግብና ጤና ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ፣ "የበረሃ አንበጣ ድንበር ዘለል የሆነ አደገኛ ነፍሳት በመሆኑ ተባዩን ከመነሻው በቀላሉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአገራት ትብብር እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው" ይላሉ፡፡

ለዚህም አጠቃላይ የበረሃ አንበጣ ሁኔታ ላይ የቀጠናው አገራት፣ የምርምር ተቋማትና የዘርፉ ተመራማሪዎች በትብብርና በቅንጅት መስራትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አባል የሆኑት ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን በበኩላቸው የበረሃ አንበጣ የሚያስከትለው ጉዳት የኢትዮጵያ ብቻ ባለመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ህብረታቸውን አጠናክረው በመከላከልና መቆጣጠር ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አንበጣን ለመቆጣጠር በቅንጅት የመስራት ተግባሩ እንዳለ ሆኖ ሰብላቸውና የግጦሽ መሬታቸው ለወደመባቸው አርሶና አርብቶ አደሮች ለጋሽ ድርጅቶችና አጋር አካላት የእለት ደራሽ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም የአፍሪካ ነፍሳት ሳይንስ ለምግብና ጤና ካንትሪ ዳይሬክተሩ ዶክተር ታደለ ተፈራ አክለዋል፡፡

አገራቱ በኢትዮጵያ መሪነት የተቋቋመውን የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በተሻለ ሁኔታ እንዲወጣ በገንዘብና በቁሳቁስ በመደገፍ የተደራጀ ተቋም ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

ዶክተር ብርሃኔ ገብረኪዳን በበኩላቸው ሁሉም የቀጠናው አገራት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የተደራጀ ተቋም መገንባትና የጋራ ጠላታቸውን በቀላሉ መዋጋት እንደሚቻል የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማንሳት ምክረ ሃሳባቸው ሰጥተዋል።

እስካሁንም በኢትዮጵያ በምዕራብ ትግራይ፣ በምስራቅ አማራ፣ በኦሮሚያ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ሶማሌ እና በምዕራብ አፋር ክልሎችና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተከስቶ በሰብልና ግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የበረሃ አንበጣው በኢትዮጵያ እሳከሁን ድረስ 420 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

የአንበጣ መንጋው ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የከፋ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም