" ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ባስመዘገቡት ውጤት ደስተኛ ነኝ "--- አትሌት ደራርቱ ቱሉ

83

አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ)ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር ባስመዘገቡት ውጤት ደስተኛ መሆኗን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።

በፖላንድ "ግዲኒያ" ከተማ ለ24ኛ ጊዜ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ አትሌቶች በአጠቃላይ ውጤት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።


የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህን ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላትን ለማበረታታት የገንዘብ ሽልማት () ሰጥቷል።

በማበረታቻ ሽልማቱ ላይ የተገኘችው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አትሌቶቹ በቂ ጊዜ ወስደው ልምምድ ሳያደረጉ የተሳተፉበት ውድድር መሆኑን አመልክታለች።

በአጭር ጊዜ ልምምድ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ መቻል የሚያኮራ ድል መሆኑን ገልጻ፣ ''በውድድሩ አትሌቶች ባስመዘገቡት ውጤት ደስተኛ ነኝ '' ብላለች።


በውድድሩ ላይ የተወሰነ የቴክኒክ ችግር መታየቱን ጠቁማ፣ በቀጣይ አሰልጣኞችና አትሌቶች ከዚህ ልምድ ወስደው የእርምት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስባለች።


በተለይ አሰልጣኞች ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን ምክር መስጠትንም መረሳት እንደሌለባቸው ነው ያስገነዘበችው።

ፌዴሬሽን ይህን ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት 280 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ እንደየውጤታቸው የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።


በሽልማቱ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ብሔራዊ ቡድኑን ይዘው የተጓዙ አሰልጣኞች ብቻ ሳይሆኑ በግል ሲያሰለጥኑ የነበሩ አሰልጣኞችም የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ኢትዮጵያ በፖላንድ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው፤ በወንዶች ደግም አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ እያንዳንዳቸው የነሀስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በቡድን በሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ፤ በወንዶች ደግሞ የብር ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ነው ማጠናቀቅ የቻሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም