የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሁለት አዳዲስ ዕዞችን አደራጀ

146

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2013(ኢዜአ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚሰጠኝን ግዳጅ በፍጥነት ማከናወን ያስችሉኛል ያላቸውን ተጨማሪ ሁለት ዕዞች ማደራጀቱን አስታወቀ። 

አዲሶቹ ዕዞች በዚህ ዓመት ወደ ስራ ይገባሉም ተብሏል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ እና የሠራዊቱ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የኦፕሬሽናል ጉዳዮች ኃላፊ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጦር ኃይል አዛዦቹ በመከላከያ ሠራዊት የለውጥ ስራዎች፣ በሠራዊቱ አደረጃጀትና በወቅታዊ የሠላምና ጸጥታ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሠራዊቱ የሚሰጠውን ግዳጅ በፍጥነት ማከናወን እንዲችል ሁለት አዳዲስ ዕዞች መደራጀታቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

ዕዞቹ በውስጥም በውጭም የሚቃጡ ጥቃቶችና ችግሮችን ፈጥነው ለመከላከል እንዲችሉ ታስቦ የተደራጁ ናቸው ብለዋል።

ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ አዲስ የተደራጁት ዕዞች ሲሆኑ የቀደሙት ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምስራቅ ዕዞች መኖራቸውንም አውስተዋል።

አዲስ የተደራጁት ዕዞች በተያዘው ዓመት ወደ ስራ እንደሚገቡና የዕዞቹም ቁጥር ከአራት ወደ ስድስት ከፍ እንደሚል ገልፀዋል።

የአዲሶቹ ዕዞች መደራጀት የአገሪቷን ሠላም አስተማማኝ ለማድረግና ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከላከልና ችግሮችን ፈጥኖ የመቆጣጠር አቅም ለመፍጠር እንደሆነም አብራርተዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ባሕርዳርን መነሻ አድርጎ የሚሰራ ሲሆን ማዕከላዊ ዕዝ ደግሞ አዲስ አበባና አካባቢዋ ላይ የሚሰራ ይሆናል እንደ አዛዦቹ መግለጫ።

ማዕከላዊ ዕዝ ያልተጠበቀ የጦርነት አደጋ ቢያጋጥም ለሌሎች ዕዞች እንደ ተጨማሪ ኃይል ሆኖ መከላከል የሚያስችል ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የዕዞቹ አደረጃጀት ከአገሪቷ ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጣ፤ አመራሩም ችሎታና ብቃትን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ዘርዝረዋል።

ሁለቱ ዕዞች ስራ ሲጀምሩ ግዳጅ በመወጣት ረገድ የነበረውን ጫና እንደሚቀንሱም ነው ያስታወቁት።

አዛዦቹ የሠላምና ፀጥታ ችግሮችን አስመልክተው በሰጡት ሀሳብም እያጋጠሙ ያሉ የፀጥታ ችግሮች ከለውጡ በፊትም የነበሩ ሰለመሆናቸው ተናግረው መንስኤ ያሏቸውን ምክንያቶች ጠቅሰዋል።

ከማንነት፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ቀበሌ አደረጃጀት ጥያቄዎች እስከ ጎሳና ሀይማኖትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶች የነበሩና አሁንም የሚስተዋሉ ችግሮች ስለመሆናቸውም ዘርዝረዋል።

ይህን ለፖለቲካ አጀንዳቸው ተጠቅመው ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲገባ ለማድረግ የሚሰሩ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ችግር በሚከሰትባቸው አካባቢዎች አሁን አንፃራዊ ሠላም ስለመኖሩና ሠራዊቱ ሕግ ማስከበርን የመጀመሪያ ስራው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።

ለአብነትም ቅማንት አካባቢ የነበረው ግጭት ወደ ሠላማዊ ሁኔታ መቀየሩን፤ በተለያዩ ክልሎችም ግጭቶች እየቀነሱ የሠላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል።

በቅርቡ ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም ተብሎ ሲነዛ የነበረውን ወሬም የፀጥታና ደህንነት ኃይሉ መቀልበስ መቻሉን ነው የተናገሩት።

ከሠራዊቱ ተልዕኮ የመፈፀም ብቃት አንፃር ስሙን የሚያጎድፉ ኃይሎች ፍላጎታቸው የከሸፈባቸው መሆናቸውንም ነው የገለፁት።

ሠራዊቱ ሕዝብን ከጥቃት ለመከላከል የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለና  ሕግና ስርዓት የማስከበር ስራዎችን ሰርቶ ውጤት እየተመዘገበ እንዳለም አንስተዋል።

በሌላ በኩል በሪፎርሙ ለሠራዊቱ ግዳጆችን መሰረት ያደረገ ስልጠና መሰጠቱንና ግዳጆችን ከየትኛውም የፖለቲካ ኃይል ገለልተኛ በሆነ መልኩ እንዲሰራ መደረጉንም አዛዦቹ አብራርተዋል።

ምድር ኃይልና ባሕር ኃይል አደረጃጀቶች ጭምር በሪፎርሙ ተደራጅተው የሰው ኃይል ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልፀው ከሳይበር ጋር በተያያዘ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከትም ኃይል እየተደራጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመከላከያ ተቋም ቴክኖሎጂ መጠቀምና የሰው ኃይል ማብቃት ላይ ዘመነኛ አሰራሮችን ተከትሎ እየሄደ መሆኑንና ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩም የዘመናዊ መሳሪያዎች ተጠቃሚ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም