የኦሞ ወንዝ ባስከተለው ጎርፍ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ድጋፍ ተደረገላቸው

141

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 9/2013 (ኢዜአ) የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ በተከሰተ ጎርፍ ከቀያቸው ለተፍናቀሉ 20 ሺህ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ድጋፍ አደረገ።

ሚኒስቴሩ ከታዋቂ ግለሰቦችና ከአርቲስቶች ያሰባሰበውን ሳኒታይዘር፣ ሳሙና፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና አልባሳት ዛሬ በዳሰነች ወረዳ በመገኘት አስረክቧል።

ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ ተጎጂዎቹን የጎበኙ ሲሆን 'በቦታው የተገኘንበት ዓላማ ሕጻናትና ሴቶች ያሉበትን ሁኔታ በመመልከትና መረጃ በማሰባሰብ ሀብት በማፈላለግ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው ፕሮጀክቶች ላይ ለመስራት ነው' ብለዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች በዘላቂነት እንዲላቀቁ በሚሰሩ ስራዎች የአካባቢውን ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች በማካተት ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመሻት እንደሆነም ተናግረዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አደጋ ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱባ ራያ በበኩላቸው በመንግስትና በተለያዩ አካላት ለተጎጂዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ክልል የሴቶች ሕጸናትና ወጣቶች ቢሮም ለተፈናቃዮቹ ፍራሽ፣ ዱቄት፣ ዘይትና አልባሳትን አስረክቧል።

የክልሉ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው ክልሉ ችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ አግኝቶ እስኪፈታ ድረስ ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አርቲስት ስለሺ ደምሴ /ጋሼ አበራ ሞላ/ ተጎጂ ወገኖች ከፍ ያለ ድጋፍ እንደሚያሻቸው በመናገር ለም መሬትና ብዙ መስራት የሚችል ጉልበት ስላላችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ ሲል ምክሩን ለግሷል።

ዳያስፖራውን በመወከል መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ዮናስ ጂ አለሙ በበኩላቸው ተጎጂዎቹ ያሉበትን ሁኔታ መረዳታቸውንና በቀጣይም ከሚኒስቴሩና ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ድጋፍ በማሰባሰብ እንደሚጎበኟቸው ተናግረዋል።

በሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ የተመራው ልዑክ በሀመር ወረዳ ዲመካ ጣቢያ የተዘጋጀውን የእናቶች ማዋለጃና ማረፊያ ማዕከልም ጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም