ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ላደረገው አቀባበልና ላበረከተው አስተዋጽኦ አመሰገኑ

165
አዲሰ አበባ ሰኔ 9/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝብ ለኤትራው ፕሬዝዳንት ላደረገው አቀባበልና በቆይታቸው ወቅት ላበረከተው  አስተዋጽኦ ምስጋና አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዝዳንቱን ከሸኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ "በዚህ ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ ላይ የተሳተፋችሁ በሙሉ ምስጋና ይገባችኋል" ብለዋል። ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች፤ ከፍ ያለ ምስጋና የቸሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአዲስ አበባ አጎራባች አካባቢዎችም በፈረስ አሸብርቀው ለፕሬዝዳንቱ አቀባበል ያደረጉትን አመስግነዋል። ወደ ሐዋሳ ሲያቀኑና በከተማዋ በነበራቸው ቆይታም ነዋሪዎች ላደረጉት ደማቅ አቀባበል እንዲሁ ምስጋና አቅርበዋል። በሚሌኒየም አዳራሽ የተደረገው ዝግጅትም የጥላቻ፣ የቂም፣ የክፉ ሃሳብ ግንብ የፈረሰበትና በሁለት ህዝቦች መካከል ዳግም እንዳይናድ ጠንካራ ፍቅር እንዲገነባ ያደረግንበት ቆይታ ነበር ብለዋል። የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ምሽቱ ያማረና የሰመረ እንዲሆን ትብብርና አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል። ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም አርቲስት መሐሙድ አህመድ እና አሊ ቢራ እያመማቸው ለአገራቸው ያላቸውን የማይነጥፍ ፍቅር ስላሳዩ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም