የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን አስመልክቶ የሕግ ክፍተቶችን ለመለየት ጥናት ተጀምሯል-ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

110

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/2013 (ኢዜአ) የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን አስመልክቶ የሕግ ክፍተቶችን ለይቶ ምክረሃሳብ ለማቅረብ ጥናት መጀመሩን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።

ተቋሙ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ከመከላከልና ምላሽ ከመስጠት አንጻር ካሉት የሕግ ክፍተቶችና በአሰራር ማዕቀፎች ላይ ከአርቲስቶች ጋር ዛሬ መክሯል።

በተቋሙ የሴቶች፣ ህጻናትና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ዐቃቤ ሕግ ወይዘሪት ምዕራፍ ተስፋኢየሱስ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን ለመከላከልና ፍትህ ለመሰጠት የሚረዱ የሕግ ድንጋጌዎች አሏት።

ይሁን እንጂ በ1996 የወጣው የወንጀል ሕግ አሁን በረቀቀ መንገድ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች አንጻር ያልታዩ ድንጋጌዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንስተዋል።

በሕጉ የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን አስመልክቶ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ለመንግሥት ምክረሃሳብ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥናት መጀመሩን ነው ያብራሩት።

ጥናቱ ጥቃት አድራሾችን በሚፈለገው መጠን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ያልተቻለው ከሕግ አፈጻጸም ችግር ወይንስ ከራሱ ከህጉ    መሆኑን ለመለየት እንደሚያስችል ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።

በጥናቱ የተለዩ ክፍተቶችን በማካተት የሕግ ማሻሻያና ሌላ የሕግ ክፍተቶችን የሚሞላ አሰራር ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በሌላ በኩል ማህበረሰቡ ማስረጃዎችን ከማቅረብና ጥቃቶችን ለሕግ አካላት እንዲጠቁም ወይዘሪት ምዕራፍ ጠይቀዋል።

ችግሩን ለማቃለል ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ከሆኑ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የውይይት ተሳታፊዎች በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በማጋለጥ በኩል በማህበረሰቡ ዘንድ ክፍተት እንዳለ ይስማማሉ።

ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር ደረጀ ዘወይንየ በጾታዊ ጥቃት ላይ የሚስተዋሉ ሕጎችን ለማሻሻል ከመንግሥት ጋር በመሥራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ችግሮችን ለመፍታት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት እየተደረገ   ነው ብለዋል።

በሴቶችና ወንዶች ህጻናት ጥቃት ላይ የሚሰራው ዝም አልልም እንቅስቃሴ መሪ አርቲስት መቅደስ  ጸጋዬ መንግሥት ሕጎችን እንዲያሻሽል ግፊት እያደረጉ መሆኑን ገልጻለች።

በግንዛቤና በመረጃ እጥረት፣ በሕግ አፈጻጸም ክፍተቶችና ሌሎች ችግሮች ላይ የሚታዩት የግንዛቤና የሕግ ክፍተቶችን ለመሙላት በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አርቲስት መቅደስ ግርማ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም