የአገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ኢትዮጵያን ከጠላት የመከላከል ብቃት ፈጥረዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ

64

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/2013(ኢዜአ) የአገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጠላት የመከላከል ብቃት ፈጥረዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ገለጹ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚፈጠሩ ግጭቶች ከሕዳሴው ግድብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸውም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ከለውጡ በኋላ አብዛኞቹ ሠላም አስከባሪ ተቋማት የተፈተኑበትና መዋቅራዊ ለውጥም የተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በንግግራቸው የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጠላት የመከላከል ብቃት ላይ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ተቋማቱ በዕውቀት ላይ የተመሰረት አደረጃጀት መፍጠራቸውንና በስልጠናና በሁኔታ ትንተናም አቅማቸውን ማደራጀታቸውን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የሚሞቱ አብዛኞቹ ዜጎች ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከልና ካማሼ አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር ውስብስብ መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁንና በክልሉ የሚፈጠሩ ግጭቶች ከሕዳሴ ግድቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

ቦታው ረዣዥም ሳሮች ያሉበትና ወጣ ገባ በመሆኑ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግና ለመጠበቅ መስራቱን አድንቀዋል።

ባለፉት 20 ቀናት ከሞላጎደል አካባቢውን ለማጽዳት የተሰራው ስራ መልካም ቢሆንም የበለጠ ስራ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ሰዎች ተደራጅተው ወደ ልማት መሰማራት እንጂ ጦር ይዘው ሰው መግደል እንደሌለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም