የዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር ዛሬ ይካሄዳል

92

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) 24ኛው የዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር ዛሬ ፖላንድ ጊደንያ ከተማ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ አምስት በድምሩ 10 አትሌቶች ትወከላለች።

በሴቶች አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው፣አትሌት ነጻነት ጉደታ፣አትሌት ዘይነባ ይመር፣አትሌት አባባል የሻነህና አትሌት መሰረት ጎላ ይሳተፋሉ።

እ.አ.አ በ2018 በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በተካሄደው 23ኛው የዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች አሸናፊ የነበረችው አትሌት ነጻነት ጉደታ ውድድሩን ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ለማሸነፍ ትሮጣለች።

ባለፈው ዓመት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው የራስ አል-ካማይ የግማሽ ማራቶን ውድድር 1 ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን የሰበረችው አትሌት አባብል የሻነህ ውድድሩን ያሸንፋሉ ተብሎ የቅድመ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ትገኛለች።

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከኬንያዊቷ አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር ከባድ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።

ኬንያዊቷ አትሌት ባለፈው ዓመት መጨረሻ በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር 1 ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ በመግባት ሴቶች የሚሳተፉበት ውድድር ብቻ ክብረወሰን መስበሯ የሚታወስ ነው።

በወንዶች አትሌት ሃይማርያም ኪሮስ፣አትሌት አንዷምላክ በልሁ፣አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ፣አትሌት ብርሃኑ ለገሰና አትሌት ጉዬ አዶላ የሚሳተፉ ይሆናል።

የአትሌት ቀነኒሳ በቀለን የ5 ሺህ እ የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን የሰበረው ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ ውድድሩን የማሸነፍ ቅድመ ግምት አግኝቷል።

አትሌት ጉዬ አዶላና አትሌት አንዷምላክ በልሁ በውድድሩ የማሸነፍ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል እንደሚገኙ የዓለም አትሌቲክስ ገልጿል።

በወንዶች ያለፉት ሶስት ተከታታይ የዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆነው ኬንያዊ አትሌት ጂኦፍሬይ ካምዎሮር ባለፈው ዓመት በመኪና አደጋ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በውድድሩ አይሳተፍም።

የሴቶቹ ውድድር በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 6 ሰዓት የሚጀምር ሲሆን የወንዶቹ ውድድር ከቀኑ 7 ሰዓት ከ30 የሚጀምር ይሆናል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ፖላንድ ጊደኒያ ከተማ ከትናንት በስቲያ የደረሰ ሲሆን ለቡድኑ አባላት በተደረገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም አትሌቶቹ ውድድሩ በሚካሄድበት ስፍራ ልምምዳቸውን አድርገዋል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት አትሌቶች የተመረጡት በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደ የሰዓት ሟሟያ ውድድር መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

በግማሽ ማራቶኑ ውድድር በወንዶች 122 በሴቶች 105 በድምሩ 227 አትሌቶች የሚሳተፉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም