የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድሮች በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ በትብብር ለመስራት የጋራ አቅጣጫ አስቀመጡ

58

አዲስ  አበባ ጥቅምት  6/2013 (ኢዜአ) የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰላምና ፀጥታ ማስከበር ሂደት በትብብር ለመስራት የሚያስችል የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታወቁ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ወንጀል ፈፃሚና ተባባሪ ተብለው የተለዩ 504 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ታውቋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እስካሁን ያከናወንውን ስራና የቀጣይ አቅጣጫ በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል።

ከውይይቱ በኋላም  ርእሳነ መስተዳድሮቹ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የታጠቁ ሽፍቶች በዜጎች ላይ ያደረሱት ተደጋጋሚ ጥቃት የተለያዩ አካላት ፍላጎት ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም "በህወሃት የሰለጠኑና ድጋፍ የሚደረግላቸው የታጠቁ ሃይሎች" ጥቃቱን እንደፈጸሙት አብራርተዋል።

የፀረ ለውጡ አቀንቃኞች፣ ፅንፈኛ ሃይሎችና በአካባቢው የተጀመረው ለውጥ እንዲደናቀፍ የሚጥሩ ሃይሎች እጅ አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈጸመው ጥቃት በሰለጠኑና በታጠቁ ሽፍቶች የተፈጸመ ነው።

በተለይም ለጥቃቱ የህወሃት ድጋፍና እገዛ ነበረበት ብለዋል።

በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እንዳለ ሆኖ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በጋራና በትብብር ይሰራሉ ነው ያሉት።

ሁለቱ ክልሎች በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰንም በክልሉ የተስተዋለውን ችግር ለመፍታት በተለይ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።

በመተከል ዞን የታጠቁ ሽፍቶች የፈፀሙትን ድርጊት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሽፍቶችን የመደምሰስ ተግባር እንዳለ ሆኖ የወንጀሉ ፈፃሚና ተባባሪ ተብለው የተለዩ 504 ተጠርጣሪዎች እስካሁን በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይም በኮማንድ ፖስቱ እንዲሁም በሁለቱ ክልሎች የጋራ ትብብር ሰላምና ጸጥታ የማስፈን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በተካሄደው ውይይት የእስካሁኑ የጸጥታ ማስከበር ሂደት ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድሮች በልማትና ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ሂደት በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም