ሕዝብ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ተቀናጅቶ መሥራት ይገባል- የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ

95

ባሕርዳር፣ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስፈፃሚው ተቀናጅቶ ሊሠራ ይገባል ሲሉ የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አሳሰቡ።

የምክር ቤቱ አራተኛ ዙር  ስምንተኛ  ዓመት የሥራ ዘመን አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተካሄዷል።

አፈ-ጉባኤው አቶ ፍትሐነገሥት በዛብህ  በጉባኤው መድረክ እንዳሉት በከተማው የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሕዝቡ እየተማረረ ይገኛል።

በተለይም በከተማዋ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የተደራጁ ማኅበራት በወቅቱ ቦታ አለማግኘትና የሥራ አጥነት ቁጥር እየጨመረ መምጣት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

እንዲሁም የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት፣ ሕገወጥ ቤቶች ግንባታና የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ችግርም አፈ-ጉባኤው አንሰተዋል።

ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን  በሕግ አግባብ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የምክር ቤት አባላትና አመራሩ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው የባሕርዳር የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ዕድገቷን የሚመጥን ዘላቂ ልማት ይከናወናል ብለዋል።

ባሕርዳር ነዋሪዎቿና ጎብኝዎች ያለሥጋት የሚንቀሳቀሱባት ሰላም የሠፈነባት ከተማ ሆና እንድትቀጥል ሕዝቡን ባሳተፈ አግባብ እንደሚሠሩ ተናገረዋል።

የከተማዋን ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋት የሥራ ዕድል እንደሚያመቻቹም ጠቅሰዋል።

ከተማዋን የኢንቨስትመንት መዳረሻና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግም በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን ከምሁራንና ባለሀብቱ ጋር ተቀራርቦ በመፍታት ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ይሰጣልም ብለዋል።

የከተማዋን መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረት ለመፍታትና በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ኑሮን ሊቀይር የሚችል አሠራር እንደሚተገበርም አብራርተዋል።

የባሕርዳር ከተማን ሁለንተናዊ ልማት በቅደም ተከተል ለማከናወን በሚደረጉ ጥረቶችም የምክር ቤት አበላትና ኅብረተሰቡ እንዲያግዟቸውም ጠይቀዋል።

ዶክተር ድረስ ሳህሉ በከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ሆነው የተሾሙት ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነው።

የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው በምትካቸው የዶክተር ድረስ  ሹመትን በማጽደቅ የምክር ቤቱ ጉባኤ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም