የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የአፋር ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ

168

ሠመራ ጥቅምት 6/2013(ኢዜአ) የአርብቶ አደሩን ፍትሃዊ ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የአፋር ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ። 

ፓርቲው ላለፉት ሁለት ሳምንታት በየደረጃው ሲያካሂድ የቆየውን ድርጅታዊ ኮንፈረሰን ማጠናቀቁን ተከትሎበወጣው መግለጫ ኮንፍረንሱ ባለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት በሀገሪቱ የተመዘገቡ ስኬቶችና በሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በማንሳት በዝርዝር መምከሩን አመልክቷል።

በዚህም ከነበሩ የግጭት ችግሮች በመውጣት ውጤታማ አመራር  ወደ ብልጽግና ለማምጣት የሚያስችሉ አበረታችና ተስፋ-ሰጪ ጅማሮዎች እንዳሉ ተውስቷል።

እንደፓርቲው መግለጫ ከአፋር ክልል አኳያ ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት አጋር በሚል ከሀገራዊ አጀንዳዎችና ውሳኔ ሰጪነት በመገለል የበይ ተመልካች ሆኖ ቆይቷል።

ለውጡን ተከትሎ ብልጽግና ፓርቲ ከመጣ በኋላ  በሀገራዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ተገልጿል።

ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ወቅቱን ሊመጠን የሚችል ብቁና ቁርጠኛ አመራር ለመፍጠር ይረዳ ዘንድ ፓርቲው በየጊዜው ተደጋጋሚ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በየደረጃው በመስጠት በአመራሩ ውስጥ ውስጥ የተግባርና አመለካከት አንድነት ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቀዋል።

አመራሩ ከግል ጥቅምና ጎራ መደበላለቅ፣ ከሌብነትና ቡድንተኝነት በመላቀቅ የተሰጠውን ኃላፊነት በተገቢው ለመወጣት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱም ተመላክቷል።

ከከፍተኛ እስከታችኛው አመራር ድረስ ለሁለት ሳምንታት  የቆየ  ኮንፍረንስ በሁሉም የክልሉ የዞን ከተሞች ተካሂደዋል።

በኮንፍረንሱ ጥንካሬና ድክመትን በመለየት በተደረገ ሂስና-ግለሂስ ከፍተኛ ችግር በነበረባቸው ሁለት  አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን በመግለጫው ተመላክቷል።

እርምጃ የተወሰደባቸው አመራሮች አቶ አህመድ መሃመድ ቦዳያ ከስራ-አስፈጻሚነትና ከብልጽግና ምክር ቤት አባልነት   ሌላው አቶ አሊ ሁሴን ኡመር እንዲሁ ከፓርቲው ምክር ቤት አባልነት ማሰናበት መሆኑ ተጠቅሷል።

እነዚህ አመራሮች  ቡድንተኝነትና በማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ የተለያዬ ኢ-መደበኛ አደረጀጃት በመፍጠር እንዲሁም ጎሰኝነትና ሙስና ውስጥ በመዘፈቅ የተጣለባቸውን ኃላፈነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው እርምጃው እንደተወሰደባቸው ተገልጿል።

የኮሮና ቫይረስ፣  የጎርፍ አደጋና የአንበጣ መንጋን  በመከላከል በክልሉ የአርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራ ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።

በማዕድን፣ ሰብልና እንስሳት ሃብት ላይ እንደሚሰራም  ተመላክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም