ከመንግስት ጎን ሆነው የጥፋት ሀይሎችን እንደሚታገሉ የአምቦ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ

57

አምቦ፣ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) ሀገርን የማተራመስ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሀይሎችን ለመታገል ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚታገሉ የአምቦ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ፡፡

ከ600 በላይ ለሚሆኑ የብልጽገና ፓርቲ ደጋፊ ወጣቶች በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ በአምቦ ከተማ ለአራት ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ትናንት ተጠናቋል፡፡

ወጣቶቹ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን  ጥረት እንደግፋለን ብለዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የኪሶሴ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ደሚሴ ከበደ በሰጠው አስተያየት እኛ ወጣቶች አንድነታችንን አጠናክረን ከመንግስት ጎን በመቆም ለሀገራችን ሰላም የሚፈለግብንን ድርሻ እናበረክታለን ብሏል።

 "እኛ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ለሚናፈሱት  የአሉባልታ ወሬዎች ጆሮ ሳንሰጥ ራሳችንንና አካባቢያችንን እንጠብቃለን"  ሲል  አክሏል።

በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለአገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ ከሆኑ በውጭ ሀገር ሆነው አሉባልታ ከማናፈስ ይልቅ አገር ቤት ገብተው መታገል አለባቸው ያለችው ደግሞ የቶርበን ኩታዬ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አበበች ሚሊዮን ናት፡፡

"መንገድ በመዝጋትና ድንጋይ በማስወርወር ስልጣን አይገኝም" ብላለች፡፡

ወጣቱ አንድነቱን አስተባብሮ ይህንን ድርጊታቸውን ሊያስቆም እንደሚገባም አመልክታለች፡፡

የሰንቀሌ ፋሪሲ ነዋሪ ወጣት አበራ መረራ በበኩሉ በስልጠናው የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቱን ጠቅሶ የተገኘውን ለውጥ በመደገፍ ከብልጽግና ፓርቲ ጎን እንደሚቆም ተናግሯል፡፡

የአምቦ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈትቤት ሃላፊ አቶ ሐጫሉ ገመቹ እንደገለፁት በከተማዋ ከስድስቱም ቀበሌዎች የተወጣጡ የተጀመረውን ለውጥ የሚደግፉ ከ600 በላይ ወጣቶች በስልጠናው ተሳትፈዋል።

 የስልጠናው ዓላማም ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ የሚያደናቅፉ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ወጣቶች የተሟላ ግንዛቤ ይዘው ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም