የባህርዳር ከተማ ምክርቤት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሾመ

163

ባህርዳር፣ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ጎሹን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

የባህርዳር ከተማ ምክርቤት 4ኛ ዙር  8ኛ ዓመት የስራ ዘመን አስቸኳይ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ እየተካሔደ ነው።

የቀድሞው የባህርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ዶክተር ማህሪ ታደሰ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክርቤቱ በአስቸኳይ ጉባኤው በምትካቸው አዲስ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሾሙ  ተገልጿል ።

አዲስ የተሾሙት ዶክተር ድረስ ሳህሉ የረጅም ጊዜ የሃላፊነት ልምዳቸውን በመጠቀም የከተማዋን እድገት ለማፋጠን የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ በጉባኤው ተገልጿል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጂኦግራፊና ኢንቫይሮመንታል ጥናት ከሃሮማያ ዩኒቨርስቲ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአመራርና መልካም አስተዳደር ከኢትዮጰያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መውሰዳቸውን በዚሁ ጊዜ ተጠቁሟል።

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በስራ አመራር ፍልስፍና ከቻይና ያገኙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለከተማዋ እድገት የሚበጁ ጠቃሚ ተግባራት ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ቀደም ሲል በምዕራብ ጎጃም ዞን የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊና በክልሉ የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ አማካሪ በመሆን ሰርተዋል።

ምክርቤቱ በተጨማሪም አቶ አላዩ መኮነን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አድርጎ ሾሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም