ማዕድናትን በማውጣት ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፆ እንዲያበረክት ለማድረግ እየተሰራ ነው... የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር

81

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2013(ኢዜአ)ማዕድናትን በማውጣት ረገድ ያሉ ችግሮች ተፈተው ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፆ እንዲያበረክት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ። 

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሱማሌ ክልል ኦጋዴን የኢላላ እና ካሉብ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ማውጫ ስፍራን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች  ተገኝተዋል።

አገሪቱ ከዓመታት በኋላ ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት በአመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር አገኝበታለው ብላ የወጠነችው  የካሉብ እና ሒላላ ነዳጅ ማውጣት የሚካሄድበትን ቦታ እስካሁን ወደ ምርት መግባት አልቻለም።

ኢንጂነር ታከለ የተፈጥሮ ጋዝና ድፍድፍ ዘይት ልማት ያለበትን የስራ እንቅስቃሴ ሁኔታ ለመመልከት በስፍራው ተገኝተዋል።

በጉብኝታቸው ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝተው እስካሁን በሙከራ ደረጃ ያለውን ልማት ወደ ምርት ማስገባት ስለሚቻልበት ሁኔታ ተመካክረዋል።

በዚህም ከሁለት ዓመት በፊት ሲካሄድ የቆየው የሙከራ ስራ ወደ ምርት ሊገባ ያልቻለበትን ምክንያትና ወደ ምርት እንዲገባ ለማድረግ ምርቱን የሚገዛ አካል እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።

ኢንጂነር ታከለ ይህንን ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀው፤ አሁን እየሰራ ያለው ኩባንያ ያለበት ውስንነት ላይ በማገዝ ወደሚፈለገው ምርት ለማስገባት ጥረት ይደረጋል ብለዋልዋል።

ይህን በማድረግም ወደ ምርት እንዲገባ እና ህዝቡ የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት ጥናትን መሰረት አድርጎ እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

አሁን ያለው ሁኔታ እንዲቀየር ሌሎች ተወዳዳሪ ተጨማሪ ኩባንያዎች እንዲገቡ እና በዚህም እርስ በእርሳቸው ተወዳዳሪ እየሆኑ ምርቱ እንዲያድግ እና ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ እውቀትና ልምድ እንዲቀስሙ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ማዕድናትን በማውጣት ረገድ ያሉ ችግሮች ተፈተው ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋፆ እንዲያበረክት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም አጽንኦት ሰተዋል።

በኢላላ እና ካሉብ የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ማውጫ ስራውን የሚከውነው የፖሊ-ጂሲኤል ኩባንያ ተወካይ ኢንጅነር ግርማ ካሳዬ በበኩላቸው በስራ ሃላፊዎቹ የተደረገው ጉብኝት በቀጣይ የስራ እንቅስቃሴያቸው በተሳካ ሁኔታ እንዲሄድ እድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

ለስራው መቀዛቀዝ የኮሮና ወረሽኝ መከሰት አንዱ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ይህ ተስተካክሎ ውጤት እንደሚመጣ ተናግረዋል።

ላለፉት 40 አመታት የተለያዩ ኩባንያዎች በኦጋዴን ሸለቆ የተፈጥሮ ነዳጅ ፍለጋ ሲያካሒዱ ቆይቷል።

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ1955 እስከ 1991 ባሉት ዓመታት 46 ጉድጓዶች ተቆፍረው በርካታ የሐይድሮካርቦን ምልክቶች እና በካሉብ እና ሒላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቶች መገኘታቸው ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም