የሚጠበቅብንን ግብር በወቅቱ እየከፈልን ነው---የሑመራ ከተማ ግብር ከፋዮች

71
ሁመራ ሀምሌ 8/2010 የሚከፍሉት ግብር ተመልሶ ልማት ላይ እንደሚውል በማመን የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በወቅቱ እየተወጡ መሆናቸውን በሑመራ ከተማ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ገለጹ፡፡ የከተማው ነዋሪና በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ በሪሁ መረሳ " እኔ በፍላጎቴ ደስ እያለኝ ነው ግብር የምከፍለው "ብለዋል። ከሚያከያከራዩተ አምስት የመኖሪያ ቤት ክፍሎችን አምና 2 ሺህ 500 ብር   ግብር ከፍለው እንደነበርና ዘንድሮም የተጠየቁትን 3 ሺህ 500 ብር ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል። ዘንድሮ የተጣለባቸው የግብር ተመኑ ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ነው" ያሉት ደግሞ በከተማው በምግብ ዝግጅት ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ አልማዝ አረጋይ ናቸው። " በተወሰነልኝ ግብር መሰረት ባለፈው ዓመት 3 ሺህ 550 ብር ከፍያለሁ " ያሉት ወይዘሯዋ፣ዘንድሮም ከአምና 300 ብር ጭማሪ በማሳየት የተጣላብኝን በመፈጸም ግዴታቸውን በወቅቱ መወጣታቸው ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ያለ አስፋልት መንገድና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ከሚከፍሉት ግብር  በመሆኑ እሳቸውን የሚጠበቅባቸውን በተገቢው በመፈጸም ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ወይዘሮ አልማዝ አውስተዋል። በችርቻሮ የጨርቃጨርቅ ንግድ ስራ የተሰማራው  የከተማው ነዋሪ ወጣት አብራሃ መስፍን  በበኩሉ" መጀመሪያ የተተመነልኝ ግብር በጣም ተጋንኖ ነበር  ሲል አስታውሷል፡፡ ወጣቱ ባቀረበው ቅሬታ  መሰረት ችግሩን በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ታይቶ ከ5 ሺህ ብር ወደ 3 ሺህ ብር ዝቅ እንዲል በመደረጉ ያለምንም ቅሬታ የሚጠበቅበትን ግብር መክፈሉን ተናግረዋል። የከተማው አስተዳደር ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሙዘይ በላይ እንዳሉት በከተማው ከሚገኙ 5 ሺህ 140 ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በተያዘው በጀት ዓመት 7 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ግብር ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ከከተማው ግብር ከፋዮች ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ 800 ሺህ ብር የሚጠጋ ግብር መሰብሰቡን አመልክተው " የከተማው ነጋዴ የሚጠበቅበትን ግብር ለመክፈል እያደረገ ያለውን ጥረት የሚመሰገን ነው "ብለዋል። በከተማው በሁለት ዙር በተደረገ  የግብር የአወሳሰን ጥናት አብዛኛው ነጋዴ በግብር አወሳሰኑ ላይ ደስተኛ መሆኑን ጠቁመው በከተማው 154 ነጋዴዎች ቅሬታ አቅርበው እንደነበርና ከመካከላቸው የ94  ነጋዴዎች የግብር ተመኑ እንደተሻሻለላቸው አመልክተዋል፡፡ 60 ነጋዴዎች ደግሞ የተተመነላቸው ግብር ፍትሃዊ በመሆኑ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል። ሑመራ ከተማን ጨምሮ  በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ከሚገኙ ግብር ከፋዮች በተጠናቀቀው  በጀት ዓመት ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስገባት ታቅዶ ባለፉት 11 ወራት  52 ሚለዮን 546 ሺህ ብር መሰብሰብም ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም