በኢትዮጵያ በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረቱ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲኖራት መሥራት ያስፈልጋል--የጋራ ምክር ቤት

64

አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረቱና በአደረጃጀታቸው ጠንካራ ፓርቲዎች መፈጠር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የምክር ቤቱ አባላት ዛሬ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በውይይቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተሳትፈዋል።

ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊነት ፣የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደረጃጀት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ወቅታዊ የፖለቲካ ተቃርኖዎች የመወያያ ርዕሶች ነበሩ።

በውይይቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በመፈራረጅና በሴራ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን፣ልምዱን ለመቀየር መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።

የፓርቲዎች ግጭትን በሚፈጥሩና ህዝብን ጥርጣሬ ውስጥ በሚጥሉ የብሄርተኝነትና ሌሎች አመለካከቶች ወጥተው በፍትህ፣በነፃነት፣በዴሞክራሲና በርዕዮተ ዓለም ላይ በመመስረት መደራጀት አለባቸው ተብሏል።

አደረጃጀታቸውም በስብስብና ዘላቂነት ባለው መንገድ መሆን እንደሚገባውም ተገልጿል።

በገዥው ፓርቲ በኩልም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን  እንዲያጠናክር ተጠይቋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወዳድሮ ለማሸነፍ ብቻም ሳይሆን፤ ለሕዝብ፣ለአገርና ለቆሙለት ዓላማ ጠንካራ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል።

በመድረኩ በፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አለመግባባቶች እንደሚከሰቱ  ተነስቷል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የገጠሙ አለመግባባቶችና ተቃርኖዎች ባለፉት ዓመታት በነበረው አገዛዝ በኢኮኖሚው፣በፖለቲካውና በማህበራዊ ዘርፎች ላይ በተከተላቸው በፖሊሲ የተደገፉ ጥፋቶች መሆኑ ተወስቷል።

አለመግባባትን በውይይትና በመነጋገር የመፍታት ልምድ አለመዳበሩም የመድረኩ አንድ ሃሳብ ነበረ።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ባቀረቡት ጽሁፍ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር ከዚያ ካለፈም በፍርድ ቤት የመፍታት እንጂ፤ ጦርነት እንደ አማራጭ መታየት የለበትምብለዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማህበረሰቡ በራሱ ያዳበራቸውን ጨምሮ ህገ መንግስትን ከማሻሻል ይልቅ አፍርሶ ሌላ ህገ መንግስት መቅረጽ ተግዳሮት መሆኑም ተጠቅሷል።

አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት የተሻሻለ ይዘት ቢኖረውም፤ በአፈፃፀም ደረጃ ግን ዝቅተኛ ነው ተብሏል።ለዚህም  ማሻሻያዎች እንዲደረግበት ሐሳብ ቀርቧል።

በተለይ የአስፈፃሚ  አካል ስልጣን ጊዜ ገደብና ምርጫ በማሳያነት ቀርበዋል።

ይሁን እንጂ በህገ መንግስቱ አተገባበር የሚታዩት ችግሮች ትኩረት እንዲሰጣቸው በተሳታፊዎቹ ተጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም