በደቡብ ወሎ ዞን በአንበጣ መንጋ የሚቀንሰውን ምርት ለማካካስ የመስኖ ልማት ሥራ ይካሄዳል

44

ደሴ፣ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን በአንበጣ መንጋ ሊቀንስ የሚችለውን የመኸር ምርት ለማካካስ ከ23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመስኖ ልማቱን ለማሳካትም ባለፈው ዓመት በ55 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገልጿል።

በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬና የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ተስፋዬ መርቆርዮስ ለኢዜአ እንደገለጹት በመስኖ ልማት ሥራው ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

እስካሁን ድረስ የወረዳና የቀበሌ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመሥራት አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት በማድረግ ከ43 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ ተግባራዊ እቅንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው።

በተጨማሪም የነባር ካናሎች ጠረጋና በአዲስ መልክ ወደ መስኖ ልማቱ የሚገባ መሬት ልየታ መካሄዱን ጠቁመው በያዝነው ወር መጨረሻ መላ አርሶ አደሩን በማነቃነቅ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመስኖ ልማቱ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የአገዳ ሰብልና የቅባት እህሎችን ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ባለሙያው ከልማቱ ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግም 43 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 400 ኩንታል ምርጥ ዘር ማቅረብ ተችሏል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ መሐንዲስ ቡድን መሪ አቶ ኃይለ ሚካኤል ፈንታው በበኩላቸው በበጋ መስኖ ልማቱ ባለፈው ዓመት በ55 ሚሊዮን ብር የተጠናቀቁ 44 የመስኖ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ይገባሉ።

አዲሶቹ የመስኖ ፕሮጀክቶቹም ሰባት ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ1 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በአዲስ መልክ ለማልማት የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።

በዞኑ በአምባሰል ወረዳ የ022 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ከተማው ታደለ እንደገለጸው በቤተሰቦቹ መሬትና የሌላ ሰው መሬት በመከራየት ሁለት ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እየተዘጋጀ ነው።

አትክልትን በስፋት በማልማት በበጀት ዓመቱ እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት ከ300 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅዷል።

ባለፈው ዓመት ከሦስት ጓደኞቹ ጋር መሬት ተከራይተው በመስኖ ካለሙት አትክልትና ፍራፍሬ ግማሽ ሚሊዮን ብር በመሸጥ መጠቀማቸውን ጠቁሞ ለዘንድሮው ልማት ልምድ እንዳገኘበት ተናግሯል።

ሌላው የተሁለደሬ ወረዳ የ014 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከድር ዓለምሰገድ በበኩላቸው ዘንድሮ የተሠራው የመስኖ ፕሮጀክት 41 ሄክታር መሬት እንደሚያለማ ተነግሯቸዋል።

"ባለኝ አንድ ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የምግብ ዋስትናዬን ከማረጋገጥ ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ተጠቀሚ እሆናለሁ የሚል ተስፋ ሰንቄ እየተዘጋጀሁ ነው" ብለዋል።

በግብርና ዘርፉ ሠርተን እንድንጠቀም መንግሥት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ተደስተናል ያሉት አርሶ አደሩ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥና በደለል እንዳይሞላ ኮሚቴ አቋቁመን መሥራት ጀምረናል ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን 54 ግድቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከሁለት ሺህ በላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ከዞኑ ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም