ጀርመንና አሜሪካ ዜጎች የህክምና መመሪያዎችን እንዲያከብሩ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ

67

ጥቅምት 05/2013 (ኢዜአ) የቫይረሱን ዳግም ማገርሸት ተከትሎ ጀርመን ከፍተኛ የስጋት አካባቢዎች ላይ ተጨማሪ ዕቀባዎች ሊደረግ እንደሚችል ቻንስለር አንጌላ ሜርክል  አስጠንቅቀዋል።

ቻንስለሯ ይሄን ያስጠነቀቁት ትላንት ረቡዕ በጀርመን ከ6 ሺህ 600 በላይ አዲስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እንዳገኘች ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነው።

ይህም ሪፖርት የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ ከተከሰተ ጀምሮ በየዕለቱ ሲመዘገቡ ከነበሩ ዕለታዊ ቁጥሮች ከፍተኛ እንደሆነ ተዘግቧል።

የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር ጄንስ ስፓህን ለሀገሪቱ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ በሰጡትቃለ ምልልስ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ ዜጎች ለጥንቃቄ ተብሎ የተቀመጡትን ህግጋት ማክበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በአሜሪካም 37 ግዛቶች የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን  የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ሀላፊ  አንቶኒዮ ፉቺ  ጠቁመዋል።

ይሁንእንጂ በሀገሪቱ የሚኖሩት ዜጎች የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር የሚያስችሉ እንደ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀምን፣ መሰባሰብን ማስወገድና ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቀሴዎችን መቀነስ የሚሉትን መመሪያዎችን እያከበሩ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ሀላፊው አክለውም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሲባል በዚህ ዓመት በሚካሄዱ የምስጋና ቀናት ላይ የሰዎች መሰባሰብ ሊከለከል ይችላል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም