በደቡብ ክልል ኮሮናን በመቋቋም ትምህርት ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው

65

ሐዋሳ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ተፅዕኖ በመቋቋም የዘንድሮውን የመማር ማስተማር ስራ ለማስጀመር የተቀናጀ ርብርብ አየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ እንደገለጹት    በክልሉ  በኮሮና  ምክንያት  6 ሺህ  የሚሆኑ የመጀመሪያ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች   ተዘግተው ቆይተዋል።

የትምህርት ተቋማቱ ላለፉት ሰባት ወራት ዝግ ሆነው በመቆየታቸው ተማሪዎች ለሥነ ልቦናና ለሌሎችም ማህበራዊ ጫና መጋለጣቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም  በየደረጃው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ዝግጁ  በማድረግ 4 ነጥብ 1ሚሊዮን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ    የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ኮቪድ 19ኝን እየተከላከሉ የትምህርት ሂደቱን ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት አቶ ማሄ በዚሁ መሰረት በክልሉ የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 9/2013 ማስተማር እንዲጀምሩ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።

በዚህ ረገድ የትምህርት ቤቶችን ቅድመ ዝግጅት የሚገመግሙ ግብረ ሃይሎች በየደረጃው ተቋቁመው በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ለሒደቱ ስኬታማነት ከማዕከል እስከ ወረዳ የሚገኙ የጤናና ትምህርት ዘርፎች ተቀናጅተው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ኃላፊው አብራርተዋል።

በክልሉ ለሚገኙ ተማሪዎች 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ከትምህርት ሚኒስቴር መፈቀዱን ገልጸው በቅርቡም ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተረከቡትን 600 ሺህ ማስክ ከዛሬ ጀምሮ ለትምህርት ቤቶች እንደሚሰራጭ  ተናግረዋል።

በኮሮና  ዙሪያ በህዝቡ ዘንድ የሚታየውን መዘናጋት እንዲቀረፍ ሁሉም አካል ተሳትፎውን እንዲያጠናክር አቶ ማሄ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም