በትግራይ ምእራባዊ ዞን ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው

63
ሁመራ ሀምሌ 8/2010 በትግራይ ምእራባዊ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በተለያየ የሰብል ዘር የመሸፈን ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የዞኑ እርሻና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የስነ አዝርእት አስተባባሪ አቶ ተክለማሪያም ነጋ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ በ2010/11 የምርት ዘመን ሰሊጥን ጨምሮ በሌሎች ሰብሎች ከሚለማው መሬት 10 ነጥብ 4 ሚልዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም ከ554 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች የመሸፈን ስራ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ እስከ ሓምሌ ወር መግቢያ ድረስ በተካሄደው የእርሻ ስራም ከ123 ሺ 563 ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም የሰሊጥ ዘር እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ከሰሊጥ ሰብል ቀጥሎም በአካባቢው ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ባለው የማሽላ ዘር መሸፈኑንም ተናግረዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ በምርት ዘመኑ ከ143 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማሰራጨት የታቀደ ሲሆን፣ እስከ ሐምሌ ወር መግቢያ ድረስ ከ27 ሺህ 750 ኩንታል በላይ መሰራጨቱን ገልጸዋል። እንደ አስተባባሪው ገለፃ በዞኑ የሚካሄደው የእርሻና የዘር ስራ እንዲሁም የግብአት ስርጭት በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዞኑ የቃፍታ-ሑመራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ይብራህ ዮሐንስ እንዳሉት ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ‘‘ባለፈው አመት ማዳበርያ አልተጠቀምኩም ነበር፤ በዚህ አመት ግን ምርጥ ዘር እና ማዳበርያ ተጠቅሚያለሁ፤ ያለኝ ሁለት ሄክታር  ማሳ የግብርና ፓኬጆችን በመጠቀም በዘር ሸፍኛለሁ‘‘ ብለዋል። በወረዳው በግብርና ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ተክላይ ደስታ በበኩላቸው ‘‘ካለኝ 50 ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉን ምርጥ ዘርና ማዳበርያ ተጠቀሜ በሰሊጥ ዘር ሸፍኛለሁ‘‘ ብለዋል። በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ባለፈው አመት በተለያየ የሰብል ዘር ከተሸፈነው መሬት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ የሚታወስ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም