በዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ኃላፊነታችንን እንወጣለን- ባለድርሻ አካላት

87

ነቀምት ጥቅምት 03/2013 (ኢዜአ) በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ከሶስት ዞኖች የተውጣጡ ባለድርሻዎች አስታወቁ ።

ከምሥራቅ፣ ምዕራብና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተውጣጡ  የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣የአስተዳደርና  የጸጥታ አካላት በዩኒቨርስቲው በተዘጋጀ የሰላም እቅድ ላይ ትላንት መክረዋል ።

ባለድርሻ አካላቱ ባካሄዱት ውይይት በዩኒቨርሲቲው  የተዘጋጀው የሰላም እቅድ በተቀናጀ አግባብ ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ።

በዩኒቨርስቲው በ2013 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል ።

በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነኢየሱስ ማዕከላዊ ሲኖዶስ የነቀምቴ የክርስቲያን ማሰልጠኛ ዳይሬክተር ቄስ አስፋው ተርፋሣ በሰላም እቅዱ የተቀመጠውን የሀይማኖት አባቶች ድርሻ ለመፈጸም አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

ተማሪዎች ከአልባሌ ተግባር ተቆጥበው ለትምህርታቸው ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ የማስተማር፣ የመምከርና የመገሰጽ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል ።

"ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው  አንድነታቸውን አጠናክረው በወንድማማችነት መንፈስ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ የድርሻችንን እንወጣለን " ያሉት ደግሞ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የኦዳ ቡሉቅ የአባ ገዳዎች ሕብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ደቻሣ ወዳጆ ናቸው ።

"ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ስነምግባር በማክበር የመጡበትን አላማ እንዲያሳኩ ምክርና ድጋፍ እንሰጣለን" ብለዋል ።፡

የነቀምቴ ከተማ የሙስሊሞች ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ  ናስር ኑሩ  በበኩላቸው " ተማሪዎች ከሰላም ውጭ ተልዕኮ ላለው ለማንም አካል መጠቀሚያ ሊሆኑ እንደማይገባ ተናግረዋል ።

ተማሪዎች ትኩረታቸውን ለትምህርታቸው ብቻ በማድረግ በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የድርሻቸውን እንዲወጡ የማድረግ ኃላፊነታቸውን አንደሚወጡ አመላክተዋል ።

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስጌን "በዩኒቨርስቲው የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ያለ ምንም የፀጥታ ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራ የተቃና እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ለማስፈን የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ያካተተ የሰላም እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

"በእቅዱ ላይ ተወያይቶ ለተግባራዊነቱ የጋራ አቋም ለመያዝ የምክክር መድረኩ  መዘጋጀቱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም