ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የ9 አገሮችን አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

102

ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ  በኢትዮጵያ የተሾሙ የዘጠኝ  አገራትን  አምባሳደሮች  የሹመት ደብዳቤ  ዛሬ ተቀበሉ።

ፕሬዚዳንቷ የሹመት ደብዳቤያቸውን ከተቀበሏቸው አምባሳደሮች ሰባቱ የአውሮፓ ሲሆኑ፣ሁለቱ ደግሞ የአፍሪካ አገሮች ናቸው።

ፕሬዚዳንቷ ከሁሉም አምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ቀይታ በኢትዮጵያ ስላለው ሁለንተናዊ ለውጥና የሁለትዮሸ ግንኙት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ብሄራዊ ጥቅሟን በሚያስከብርና በሚያስቀጥል መልኩ እንደምትሰራም መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

በተለይም በንግድ፣ኢንቨስትመንት፣በፆታ እኩልነት፣በትምህርት፣በጤናና መሰል ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጐት እንዳላት ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል ።

አምባሳደሮቹ በበኩላቸው የወከሏቸው አገሮች በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ እንደሚደግፉና በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ትስስር ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የአየርላንዷ አምባሳደር ኒኮላ አነ ብረናም አገራቸው በኢትዮጵያ ቀጣይ የሚካሄደውን ምርጫ ጨምሮ በጤናና ኮቪድ 19 መከላከል ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባኬር በበኩላቸው የኔዘርላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ኢንቨስትመንት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትንን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት  የአገራቸው ኩባንያዎች  ከ30 እስከ 35 ሺህ ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የፈጠሩትን ሥራ ለማስፋት ጥረት እንደሚያደርጉ  አምባሳደር ሄንክ ተናግረዋል።

ስዊድን የአውሮፓ ህብረት ጠንካራ አባል እንደመሆኗ ሁሉ፤ በኢትዮጵያና በህብረቱ መካከል ያለውን የባለብዙ ወገን ግንኙነት ለማሳደግም ድርሻዋን ትወጣለች ያሉት ደግሞ አምባሳደር ሃንስ ሄነሪ ሉንድክቪስት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም