በሁሉም የግብርና ዘርፎች በዘመናዊ አሰራር በመታገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው--- የኦሮሚያ ክልል

78

መቱ፣ ጥቅምት 2/2013 (ኢዜአ) በሁሉም የግብርና ዘርፎች በዘመናዊ አሰራር በመታገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች በኢሉአባቦር ዞን የግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ማሳን ጎብኝተዋል።


በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ እንደገለጹት  በሰብል ልማት ዘርፍ በዘመናዊ አሰራር የታገዘ የኩታ ገጠም እርሻ በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በተለይም ስንዴን በብዛትና በጥራት በማምረት ከውጭ የሚገባን ምርት ለማስቀረት አቅጣጫ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ ሰብል አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በተያዘው መኽር ወቅት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ኩታገጠም ማሳ ላይ የሰብል ልማት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኩታ ገጠም እየለማ ያለው ማሳ ካለፈው ተመሳሳይ የምርት ወቅት በ800 ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው አመልከተዋል።

በቡና ልማት ዘርፍ በክልሉ በ175 ወረዳዎች ምርታማነትን ለማሳደግና የጥራት ደረጃን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያ ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሄክታር የሚገኘውን ሰባት ኩንታል የቡና ምርት ወደ 15 ኩንታል ማሳደግና ጥራቱን ማሻሻል የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በስፋት መጠቀምና ያረጀ የቡና ዛፍ ጉንደላን ተግባራዊ ማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አርሶ አደሩ የአካባቢውን አመቺነት በመጠቀም ከቡናና ሰብል ልማት ጎን ለጎን በማር ምርት በስፋት እንዲሳተፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘርፉ ለሚሳተፉ አርሶ አደሮች ከ300ሺህ በላይ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ምክትል የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።


በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ አርገታ በጉብኝቱ በኢሉአባቦር አርሶ አደሮች በኩታገጠም ማሳ እየተካሄደ ባለው የደን፣ የቡና፣ ቅመማ ቅመምና ንብ ማነብ ጥምር ግብርና ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል።

"ሙዝ፣ ከቡናና ሌሎች ፍራፍሬዎች ጋር በጥምር ለምተው የተገኘውን  ውጤት ለመጀመርያ ጊዜ በማየቴ የበለጠ ተደስቻለሁ" ብለዋል።


"የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ለማር ምርት ያለውን አስተዋፅኦ ከውጤታማ አርሶ አደሮች ልምድ አግኝቻለው" ያሉት ደግሞ ከአባይ ጮመን ወረዳ የመጡ አርሶ አደር ፍቃዱ አጋ ናቸው።

አርሶ አደሮቹ ወደ መጡበት ሲመለሱ ያገኙትን ልምድ ለሌሎች በማዳረስ ልማቱን ለማስፋፋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢሉአባቦር ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሺፋ ጣሂር በዞኑ አርሶ አደሩ በዘመናዊ አስተራረስ ልማቱን በማከናወን ተጠቃሚነቱን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።


አርሶ አደሮች ከቡናና ቅመማ ቅመል በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፍራፍሬዎች በስፋት በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሙያ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተያዘው መኽር ወቅት ከ6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ እየለማ ካለው ሰብል ከ180 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክታል።

:

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም