በኢትዮጵያ የሳተላይት መገጣጠሚያና ፍተሻ ማዕከል ይገነባል

53

አዲስ አበባ፣መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሳተላይት መገጣጠሚያና ፍተሻ ማዕከል እንደሚገነባ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የህዋ ሳምንት ማጠቃለያ መርሃ ግብር 'ሳተላይት ለላቀ ህይወት!' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፣ ዘርፉን በተመለከተ በቀረበው ጽሁፍ ላይ ውይይት ተደርጓል።  

በውይይቱም ኢትዮጵያ ከመስኩ የምታገኘው ጥቅም፣ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃና ቀጣይ ሥራዎች ላይ  ሀሳብ ቀርቧል።

በዘርፉ የላቀ ደረጃ የደረሱ አገሮች ባለፉት 60 ዓመታት ከሳተላይት ቴክኖሎጂ  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ማግኘታቸው ተጠቅሷል።   

ቴክኖሎጂው ባለፉት አራት ዓመታት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው የተገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የሯሷን ሳተላይት ማምጠቋ ተገልጿል።   

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ወደ ህዋ የመጠቀችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት የምትልከው መረጃ በተለያዩ አካላት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ከዚህ ባለፈም ተጨማሪ የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።   

አገሪቷ ከመስኩ የምታገኘውን ጥቅም ለማስፋት የሳተላይት መገጣጠሚያና መፈተሻ ማዕከል ለመገንባት ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ የአዋጭነት ጥናት ተጠናቋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የቦታ ልየታም እየተካሄደ ነው ብለዋል። 

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ እስከ 500 ኪሎግራም የሚመዝን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በማምረትና በመፈተሽ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚደረግ  አስታውቀዋል።  

ፕሮጀክቱ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመታት እንደሚፈጅ የተናገሩት አቶ አብዲሳ፣ በማዕከሉ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።  

በዚህም በዩኒቨርሲቲዎች በሁለተኛና ሦስተኛ  ደረጃ ዲግሪ ትምህርት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የሳተላይት መረጃ ፍላጎት ለማሟላት የመሬት መረጃ መቀበያ ጣቢያ በአራት ወራት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ገልጸው፣ ይህም ከአምስት ሳተላይቶች መረጃ እንደሚቀበል ተናግረዋል።  

ዓለም አቀፉ የህዋ ሳምንት በዓለም ለሃያ፣በኢትዮጵያ ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ ተከብሯል።   

በሳምንቱ የህዋ ሳይንስ ገለጻ፣የበጎ አድራጎት ሥራዎችና ደም ልገሳ መርሐ  ግብሮች መካሄዳቸውን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም