የኢትዮ- ሱዳን የጋራ ወታደራዊ ውይይት እየተካሄደ ነው

66

ባህርዳር መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) 31ኛው የኢትዮ- ሱዳን የጋራ ወታደራዊ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ልዑካን መሪ ብርጋዴል ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ የውይይት መድረክ በድንበር አካባቢ በሚስተዋሉ የፀጥታ አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ የጋራ ውይይት ችግሮቹን በማንሳት በመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ስምምነት ለመድረስ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ልዑካን  መሪ ሜጀር ጄኔራል ሳላህ አብዴላ በበኩላቸው በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የሁለቱን ሃገራት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ውይይት ለማካሄድ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

"ከውይይቱ በኋላም ስምምነት ላይ በምንደርስባቸው ጉዳዮች ላይ ተመስርተን በድንበር አካባቢ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በኛ በኩል በቁርጠኝነት እንደምንሰራ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን" ብለዋል።

ለተደረገላቸው መልካም የሆነ አቀባበል የሁለቱን ሀገራት ወንድማማችነት  የሚያሳይ መሆኑን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ እርዚቅ ኢሳ  በመድረኩ ባደረጉት ንግግር  ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር  እንዳላቸው ገልጸዋል።

በባህል፣ በኃይማኖትና በሌሎች መስተጋብሮች ያለው እንቅስቃሴ የሁለቱን አገራት ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት 300 ኪሎ ሜትር ርዝመት ከአማራ ክልል ጋር በድንበር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፊ የኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት አካባቢ መሆኑ ተናግረዋል።

በቅርቡም የሱዳን ከፍተኛ ባለሃብቶች ወደ አማራ ክልል መጥተው በሰሜን ተራሮች አካባቢና ጎርጎራ ሁለት ቢሊዮን ብር በመመደብ ወደ ልማት ለመግባት መወሰናቸውን አውስተዋል።

በቆይታቸውም የአማራ ክልል መንግስት ለውይይት መድረኩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አቶ እርዚቅ አስታውቀዋል።

የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ልዑካን ጣና ሃይቅ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችንና የጢስ አባይ ፏፏቴን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም