ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ

232

አዲስ አበባ መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባው ስድስት የተለያዩ አጀንዳዎችን ተመልክቷል።

የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ለቋሚ ኮሚቴ ከመራቸው አዋጆች መካከል አንዱ ነው።

አዋጁ በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል ነው የተባለው።

የወንጀል ምርመራ፣ ክስ፣ የፍርድ ሂደት፣ የውሳኔ አፈጻጸምና በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጡ የሰብአዊ መብቶችን ማክበር በረቂቅ አዋጁ ዓላማዎች ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

በተጨማሪም የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ እውነትን ማውጣት እንዲችል፣ ውጤታማና ፍትሐዊ እንዲሆን ማስቻልና የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በረቂቅ አዋጁ ዓላማ ውስጥ ተካተዋል።

ምክር ቤቱ የተለያዩ ምዕራፎችን፣ ጠቅላላ ድንጋጌዎችንና አንቀጾችን ያካተተውን ይህን ረቂቂ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በኢትዮጵያና በራሽያ ፌዴሬሽን መንግሥት መካከል የኒውክለር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል የተደረገውን ሥምምነት ለማጽደቅ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅም ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ተመልክቷል።

ረቂቅ አዋጁ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ሰላማዊ የኒውክለር ኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ለላቀ ትብብር አስተዋጽኦ ለማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በደረሱት ሥምምነት መሠረት የተዘጋጀ ረቂቅ ነው።

ኢትዮጵያ የአውቶሚክ ኃይል መሠረተ ልማት ለማቋቋምና ለማጎልበት ለምታከናውነው ተግባር ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ላይ አገራቱ በትብብር እንደሚሠሩ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል። 

ምክር ቤቱ ይህን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲታይ መርቷል።

ምክር ቤቱ ሌላው በዛሬው ውሎው የተመለከተው ረቂቅ በአዋጅ ቁጥር 166/1952 የወጣውን የንግድ ሕግ መጽሐፍ 1፣ 2 እና 5ን ከጸናበት ቀን ጀምሮ የሚሽረውን የንግድ ሕግ ረቂቅ አዋጅ 2012ን ነው።

በዚሁ ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊነት ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቷል።

የተለያዩ ምዕራፎችንና አንቀጾችን ያካተተው ይህንን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅንም መርምሮ በተመሣሣይ ለቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ሥነ ሥርት ላይ ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽንም ምክር ቤቱ አድምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም