ከ5 ሳተላይቶች ከፍተኛ ጥራት ያለው መረጃ የሚቀበለው የምድር ሳተላይት መቀበያ ጣቢያ ግንባታ 50 በመቶ ደርሷል

191

አዲስ አበባ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ/ም (አዲስ አበባ) ከአምስት ሳተላይቶች ጥራት (ሪዞሉሽን) ያለው መረጃ የሚቀበል የምድር ሳተላይት መቀበያ ጣቢያ ግንባታ 50 በመቶ መድረሱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

ግንባታው ሲጠናቀቅ የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር ለተለያዩ አገሮች የሳተላይት መረጃ መሸጥ ያስችላል።


በቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ዲጅታላይዜሽን አማካኝነት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድገው የፖሊሲ ክለሳ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ዓዋጆችም እየተዘጋጁ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ እንዳሉት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የያዘውን ራዕይ በቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ዲጅታላይዜሽን መሰረተ ልማት መታገዝ አለበት።

ለዚህ ደግሞ ነባሩን የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም እየተከለሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፖሊሲዎቹን ወደ ተግባር ለመቀየር የተዘጋጁ አራት ዓዋጆችን ለማጽደቅ ለመንግሥት መቅረባቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ባለፈ ዓመት ያመጠቀቻት ሳተላይት በተያዘው ዓመት ከአምስት ሳተላይቶች ከፍተኛ ጥራት(ሪዞሉሽን) ያለው መረጃ የሚቀበል የምድር ሳተላይት መቀበያ ጣቢያ ግንባታ 50 በመቶ መድረሱን አረጋግጠዋል።

የጣቢያው ግንባታ በቅርቡ  ሲጠናቀቅ የልማት ዘርፎችን ከማቀራረብና የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር፤ ወደ ተለያዩ አገሮች የሳተላይት /ዳታ/ መረጃ መሸጥ ያስችላታል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው የሩብ ዓመት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች የሚማሩበት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዮት ግንባታ 87 በመቶ ማድረሱን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል።

እስካሁን ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎችን የሚያስተናግድ የትምህርት ሥርዓት እንዳልነበረ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኢንስቲትዩቱ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለአገሪቱ የቴክኖሎጂ እድገት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው ለማህበረሰብ አገልግሎት ለማዋል ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም