ደንበኞች እየተጠቀሙበት የሚገኘው የሞባይል አገልግሎት ቁጥር /ሲም ካርድ/ በስማቸው የተመዘገበ መሆን አለበት - ኢትዮ-ቴሌኮም

328

አዲስ አበባ መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) ደንበኞች ራሳቸውን ከቴሌኮም ማጭበርበርና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ለመጠበቅ እየተጠቀሙበት የሚገኘው ሲም ካርድ በስማቸው የተመዘገበ መሆን እንዳለበት ኢትዮ-ቴሌኮም አሳስቧል።

በርካታ የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች እየተጠቀሙበት የሚገኘው ሲም ካርድ በስማቸው ያልተመዘገበ መሆኑን ኩባንያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በመሆኑም ደንበኞች ሞባይላቸው ሲጠፋ ምትክ ሲም ካርድ ለማግኘት፣ አገልግሎታቸው በተለያየ ምክንያት ሲቋረጥ መልሶ ለማስቀጠልና የተለያዩ ድህረ-አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ሽያጭ ማዕከል ሲቀርቡ ጥያቄዎቹን ለማስተናገድ መቸገሩን ገልጿል።

ይህን መነሻ በማድረግም በስማቸው ያልተመዘገበ የሞባይል አገልግሎት እየተጠቀሙ የሚገኙ ደንበኞች የስም ዝውውር ለውጥ በማድረግ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን አሠራር ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም ደንበኞች ቀደም ሲል ሲም ካርዱን በስማቸው ካወጡት ደንበኛ ጋር በአካል በመቅረብ እንዲሁም ደንበኛው በሕይወት ከሌሉ፣ በቋሚነት ከአገር ውጭ የሚኖሩ ከሆነ አልያም በተለያዩ ምክንያቶች በአካል መገኘት ካልቻሉ ኩባንያው ለዚሁ ዓላማ ያዘጋጀውን ቅፅ በመሙላት የስም ዝውውር ማድረግ እንደሚችሉ ገልጿል።

ደንበኞች በስማቸው የተመዘገበን የአገልግሎት ቁጥር /ሲም ካርድ/ ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ በሚፈልጉ ጊዜ በኩባንያው የሽያጭ ማዕከል በመቅረብ ዝውውሩን በሕጋዊ መንገድ መፈፀም ይችላሉም ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም